ተስፋ የከሰመበት የሊባኖስ ተቃውሞ

ሰልፈኞቹ ሙዚቃ ከፍተው በአረብኛ "ታውራ፣ ታውራ፣ ታውራ" እያሉ እየዘመሩ ይደንሱ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ሰልፈኞቹ ሙዚቃ ከፍተው በአረብኛ "ታውራ፣ ታውራ፣ ታውራ" እያሉ እየዘመሩ ይደንሱ ነበር
ታትሟል

አምና በትሪፖሊ አል-ኑር አደባባይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ሰልፍ ወጥተው ነበር። ሰልፈኞቹ ሙዚቃ ከፍተው በአረብኛ "ታውራ፣ ታውራ፣ ታውራ" እያሉ እየዘመሩ ይደንሱ ነበር።

ታውራ አብዮት ማለት ነው። ወጣቶቹ ሥራ፣ የተሻለ ማኅበራዊ አገልግሎት ማግኘት ነበር ጥያቄያቸው። ሙስና ይቀረፍ ሲሉም ተደምጠዋል።

የአምናው ተቃውሞ

የአብዮቱ ዲጄ በሚል ቅጽል ስም የሚጠራው ማህዲ ካርሚህ ነው። የ30 ዓመቱ ፕሮግራመር "በሕይወቴ እንደዛ ቅጽበት ደስ ብሎኝ አያውቅም" ይላል።

እንደ ማህዲ ሁሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያን መንግሥት እንዲለወጥ የሚጠይቅ ሰልፍ በተለያዩ ከተሞች አካሂደዋል።

"ከጓደኞቼ ጋር ቡና እየጠጣሁ የሊባኖስ ሰንደቅ አላማ ይዘው የሚጓዙ ሰዎች ስመለከት ኮንሰርት የማዘጋጀት ሐሳብ መጣልኝ" ይላል ማህዲ።

ተቃዋሚዎቹ በተለያየ የኑሮ ደረጃ ያሉ፤ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታይ ናቸው። በሊባኖስ ታሪክ ከፋፋይ የነበሩ መስመሮችን ሁሉ ትተው ተሰባስበው ነበር። ለውጥ እንደሚመጣም ተስፋ አድርገዋል።

ከሊባኖስ ከተሞች ድሃ በሆነችው ትሪፖሊ ተቃውሞ ሲካሄድ ማህዲ አንድ ቤት በረንዳ ላይ ሆኖ ሙዚቃ እያጫወተ ነበር።

"እዚህ ቦታ ስቆም ማልቀስ ይቃጣኛል" ይላል ማህዲ።

መንግሥት እንደ ዋትስአፕ ያሉ መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙ ሰዎች ግብር እንዲከፍሉ ረቂቅ ማውጣቱን ተከትሎ ነው ተቃውሞው የተቀሰቀሰው።

ተቃውሞው ከዚህ ባሻገር ሙሰኛ ባለሥልጣኖች የተወገዙበትም ነበር።

ተደራራቢ ጫና

ከዓመት በፊት የተካሄደውን ይህን ተቃውሞ የሚያስታውሰው ማህዲ፤ የሊባኖስ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱ ያሳስበዋል።

"ከመቼውም ጊዜ በላይ አደባባይ መውጣት ያለብን አሁን ነው። ከዓመት በፊት ከነበረው ይልቅ አሁን ችግሩ ተባብሷል።"

ሊባኖስ ምጣኔ ሀብቷ ላሽቋል። ኮሮናቫይረስ ተጭኗታል። ወደብ አቅራቢያ ከደረሰው ፍንዳታም አላገገመችም።

2,750 ቶን የሚመዝን አለሙንየም ናይትሬት ወደብ አቅራቢያ መከማቸቱን መንግሥት ቢያውቅም ምንም እርምጃ አልወሰደም ነበር።

በፍንዳታው 200 ሰዎች ሲሞቱ ከ6,000 በላይ ሰዎች ተጎድተዋል። ከሟቾቹ መካከል ሁለት ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበት መዘገባችንም ይታወሳል።

የፈረንሳዩ ፕሬዘደንት ኢማኑኤል ማክሮን የሊባኖስ መሪዎች ማሻሻያ እንዲያደርጉ ቢወተውቱም እምብዛም ለውጥ አልተስተዋለም።

እአአ 1990 ላይ ያከተመው የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ የተፈረመ ስምምነትን ተመርኩዞ ነው የአገሪቱ አስተዳደር የተመሠረተው።

አምና ተቃውሞው ሲቀሰቀስ ሥልጣናቸውን የለቀቁት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሳአድ ሃሪሪ ወደ ሥልጣን እንዲመለሱ ይፈለጋል።

እሳቸውን ተክተው ሥልጣን የያዙት ሰው ፍንዳታውን ተከትለው ከኃላፊነታቸው ወርደዋል።

ተስፋ አለ?

ሊባኖስ አአሜሪካ እና ኢራን ሽኩቻ መሀልም ናት።

ኢራን የምትደግፈው ሄዝቦላ በሊባኖስ ከፍተኛ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ሥልጣን አለው።

ባለፈው ወር አሜሪካ በሁለት የቀድሞ የሊባኖስ ሚንስትሮች ላይ እገዳ መጣሏ አይዘነጋም። ሚንስትሮቹ ለሄዝቦላ የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋሉ በሚል ነው የታገዱት።

ከታቃሚዎቹ አንዷ ሊና ቦውበስ ነገሮች በመባባሳቸው ተስፋ አልቆረጡም። እንዲያውም ለውጥ እንደሚመጣ ያምናሉ።

"የሆነ ቦታ መጀመር አለብን። እንዲለወጥ የምንሻው 30 ዓመታት የተንሰራፋ ሙስና መሆኑን መርሳት የለብንም።"

የ60 ዓመቷ ሊና "ሁሉም ፖለቲከኞቻችን ሙሰኞች ናቸው። ከታች ጀምሮ ለውጥ መምጣት አለበት" ይላሉ።

የአሁኑን ትውልድ እንደቀደምቶቹ መግታት እንደማይቻልና ወጣቱ ድምጹን ከማሰማት ወደኋላ እንደማይል ሊና ይናገራሉ።

የሊናን ተስፋ ብዙዎች አይጋሩትም። አምና በተነሳው ተቃውሞ ተስፋ ጥለው የነበሩ አሁን ስጋት ገብቷቸዋል።

ከአገር የመውጣት አቅም ያላቸው ሊባኖስን ጥለው እየወጡ ነው።

ያለ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ሊባኖስ እንደ አገር መቆም እንደማትችል በርካቶች ይሰጋሉ።