ሊባኖስ ፡ ቤይሩት ውስጥ ባጋጠመ ፍንዳታ ቢያንስ አራት ሰዎች ሞቱ

ፍንዳታው የተከሰተው በርካታ ሰዎች በሚኖሩበት ሰፈር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፍንዳታው የተከሰተው በርካታ ሰዎች በሚኖሩበት ሰፈር ነው
ታትሟል

በሊባኖስ መዲና ቤይሩት የነዳጅ ማጠራቀሚያ ፈንድቶ ቢያንስ አራት ሰዎች ሲሞቱ 20 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት ደረሰ።

ፍንዳታው የተከሰተው ታሪቅ አል ጂዲ በተባለ ጎዳና በርካታ ሰዎች በሚኖሩበት ሰፈር ነው።

በቴሌቪዥን የተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ነበልባሉ በጠባብ ጎዳና ላይ በሚገኙ ቤቶች ጫፍ ላይ ደርሶ አሳይተዋል።

እስካሁን ድረስ እሳቱ እንዴት እንደተነሳ ያልታወቀ ሲሆን በአካባቢው የተሰማሩት የአደጋ መከላከል ሠራተኞች አሁንም ሰዎችን ከአደጋው የማዳን ሥራቸውን እንደቀጠሉ ናቸው።

ትላንትና ፍንዳታው ሲከሰት፤ እሳት አደጋ ተከላካዮች በመሰላል መኖሪያ ቤቶች ላይ ወጥተው በረዳቸው ላይ የነበሩ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ሲጣጣሩ ነበር።

አንዲት ሴት "የፍንዳታው ድምጽ ሲሰማና ቤታችን ሲንቀጠቀጥ ደነገጥን። የምንኖርበት ሰፈር ያሉ ሰዎች ባጠቃላይ መጮህ ጀመሩ። ክስተቱ ወደኋላ መለሰኝ" ብላ ትዊት አድርጋለች።

ነሐሴ ላይ በቤይሩት ወደብ አካባቢ የተከሰተው ፍንዳታ የ203 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይታወሳል። ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል። ሁለት ኢትዮጵያዊያን በአደጋው መሞታቸውን መዘገባችንም ይታወሳል።

ከነሐሴው ፍንዳታ በኋላ በአንድ መገበያያ ስፍራ የእሳት አደጋ ተከስቶ እንደነበርም ይታወሳል።

እነዚህ ፍንዳታዎች በምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ሊባኖስ ነገሮችን አባብሰዋል። አገሪቱ ኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠርም እየታገለች ነው።

ሊባኖስ ነሐሴ ላይ ከተከሰተው ፍንዳታ ገና አላገገመችም።

ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ፍንዳታው ኒውክሌር ነክ ካልሆኑ ፍንዳታዎች ባጠቃላይ ትልቁ ነው።