ሰሜን ኮርያ፡ በታሪክ ትልቁ ከተባለው ወታደራዊ ትዕይንት ምን ይጠበቃል?

ታትሟል

ሰሜን ኮርያ በታሪኳ ትልቁን ወታደራዊ ትዕይንት ለማሳየት እየተዘጋጀች ነው።

በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እንዳይስቱ፣ መሪው ኪም ጆንግ ኡንን ለማስደሰትም ለወራት ሰልጥነዋል።

መሰል ትዕይንቶች መሪው ታማኝ ወታደሮች እንዳሏቸው ማሳያ ናቸው። በትዕይንቶቹ ላይ ስህተት መስራት የማይታሰብ ነው።

ትዕይንቶቹ ለትንኮሳም ይውላሉ። የምጣኔ ሀብት ማዕቀብ ቢጣልብንም አዳዲስ ሚሳኤሎችና መሣሪያዎች አሉን ለማለት ይጠቀሙባቸዋል።

እአአ በ2018 የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተወያዩ ወዲህ፤ በሰሜን ኮርያ ወታደራዊ ትዕይንቶች ላይ ሚሳኤል አልታየም።

ባለፈው የካቲት ያካሄዱት ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ግን ሁለቱም አገሮች በአጭር ርቀት የሚወነጨፉ ሚሳኤሎች እየሞከሩ ነው።

ወታደራዊ ትዕይንቱ የሠራተኞች ፓርቲ ምስረታ 75ኛ ዓመትን አስታኮ ጥቅምት 10 ነው የሚካሄደው። ይህም ከአሜሪካ ምርጫ ጥቂት ሳምንታት ይቀድማል።

ሰሜን ኮርያ አሜሪካን ለመውጋት የሚያስችሏት መሣሪያዎች እንዳሏት እየጠቆመች ይሆን?

በትዕይንቱ ምን ይታያል?

ትርዒቱ ትልቅ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ስዑል ውስጥ የሚሠራ ድረ ገጽ ዋና አዘጋጅ ይህንኑ ያረጋግጣል።

ዋና አዘጋጁ ሊ ሳንግ ዮንግ እንደሚለው፤ ከመጋቢት ጀምሮ 32,000 ወታደሮች እንዲለማመዱ ታዟል።

"በፒዮንግያንጉ ሚሪም አውሮፕላን ማረፊያ ሁለት አዲስ መንገድና 10 አዳዲስ ሕንፃዎች ተገንብተዋል። በትዕይንቱ ላይ ባላስቲክ ሚሳኤል እና ባህር ሰርጓጅ ሚሳኤል ልንመለከት እንችላለን" ብሏል።

ከኪም ሰንግ 2ኛ ዩኒቨርስቲ 600 ተማሪዎች እና ተመራማሪዎችም በትዕይንቱ ይታያሉ። ዩኒቨርስቲው አዲስ ሚሳኤሎች የሚገነቡበት ሲሆን፤ ሰሜን ኮርያ በተመራማሪዎቹ እንደምትኮራ ለማሳየት እንደንትፈልግ ሊ ይናገራል።

የኤንኬ ኒውስ ተንታኝ ጄንግሚን ኪምእንደሚለው፤ ሰሜን ኮርያ ትዕይንት የምታሳየው ለተቀረው ዓለም መልዕክት ለማስተላለፍ ብቻ አይደለም።

"ከልጅ ልጅ የሚሸጋገር አምባገነናዊ ሥርዓት እንደመሆኑ ለአገሪቱ ዜጎች መሪያችሁ እኛ ነን ለማለት ይጠቀሙበታል" ይላል።

ጥቅምት 10 የሚካሄደው ትዕይንት በማራኪ ትርኢት እና በፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን ለማሳመን ያለመ መሆኑንም ያክላል።

ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን በማጣጣል መሪው ንግግር ሊያደርጉም ይችላሉ።

የሰሜን ኮርያ ዜጎች ጉዳይ

የ25 ሚሊዮኑ የሰሜን ኮርያ ዜጎችን ጉዳይ ብዙዎችን ያሳስባል። ዓመቱ ከሌሎች አገሮች በባሰ ለሰሜን ኮርያ ከባድ ነበር።

ሊ እንደሚናገረው፤ የወላጅ አልባና የጎዳና ተዳዳሪ ታዳጊዎች ቁጥር መጨመሩ ይሰማል።

"ደቡብ ኮርያ ውስጥ ያለን ሰዎች ባናውቅም ሰሜን ኮርያ ውስጥ የሚራቡ፣ የሚሞቱ ሰዎችም አሉ" ይላል።

ሰሜን ኮርያ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ድንበሯን ከዘጋች ወራት ተቆጥረዋል። ድንበር ጥሰው ሊገቡ የሚሞክሩ ሰዎችን ተኩሰው እንዲገድሉ ለወታደሮች ትዕዛዝ ተላልፏል።

ክትባትን ጨምሮ የተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች መገልገያ ቁሳቁሶች ከቻይና ጋር ከሚያዋስነው ድንበር ማለፍ እንዳልቻሉም ተገልጿል።

ሰሜን ኮርያ አንድም በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው እንደሌለ ትናገራለች። ሆኖም መሪው ጥብቅ ገደቦችን ለማስተግበር ከፍተኛ ስብሰባዎች እያካሄዱ ነው።

"በባህርም፣ በየብስም፣ በአየርም ወደ አገሪቱ መግባት አይቻልም። ከወታደሮች ውጪ ማንም ወደ አገሪቱ አይገባም" ይላል ሊ።

የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እንደተገታ ሊ ያስረዳል። ኮሮናቫይረስ በሰሜን ኮርያ ካልተገኘ ለምን ምጣኔ ሀብት ላይ ጫና የሚያሳድር ውሳኔ እንደተላለፈ የድንበር አካባቢ ነጋዴዎች ይጠይቃሉ።

የሰሜን ኮርያ እና ቻይና ንግድ 70 በመቶ አሽቆልቁሏል። የአገሪቱ አየር ሁኔታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል።

ኪም ጆንግ ኡን ምጣኔ ሀብቱ እንዲያገገም አገር አቀፍ ንቅናቄ እንዲጀመር አዘዋል።

ይህ ማለት ደግሞ ሰሜን ኮርያውያን ላይ የሥራ ጫና ይበረታል ማለት ነው። በእርሻና በፋብሪካ የሥራ ሰዓት ሊጨምርም ይችለል።

የአገሪቱ ሰብል ምርት ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ማወቅ ከባድ ነው። ሆኖም ወደ 11 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ እጥረት እንደገጠማቸው ይገመታል።

ሁለቱ ኮርያዎች

ሰኔ ላይ ፒዮንግያንግ ከስዑል ጋር ያላትን ግንኙነት አቋርጣለች።

በወሩ መባቻ ላይ ወደ ደቡብ ኮርያ ሊሸሽ የነበረ ግለሰብ መገደሉ ተሰምቷል። ግለሰቡ የተገደለው በስተምዕራብ ባለው ቀጠና ሲሆን፤ አስክሬኑ ተቃጥሏል።

ክስተቱ ደቡብ ኮርያውያንን አስደንግጧል። ሆኖም ሰሜን ኮርያ ውስጥ ጓደኛ ያላቸው ብዙ ናቸው።

ትራምፕ እና ኪም ኒውክሌር የማስወገድ ስምምነት ላይ መድረስ ባይችሉም እንኳን ለ70 ዓመታት የዘለቀው ጦርነት ያከትማል ብለው ተስፋ የሚያደርጉም አሉ።

ከሦስት ዓመት በፊት ሰሜን እና ደቡብ ኮርያውያን በጋራ ኦሎምፒክስ ላይ ተወዳድረዋል። ይህ ወደ ሰላም ያሸጋግራቸዋል ተብሎም ነበር።

የጋንግዋን ግዛት አገረ ገዢ ቾይ ሙን ሱን "ትልቅ ስምምነት ላይ እንደርሳለን ስንል ምንም ሳንስማማ ቀርተናል። በስፖርትና በባህል ሰላም ለማውረድ መሞከር አለብን" ብለዋል።

አገረ ገዢው በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ በተባበሩት መንግሥታት በኩል የሰላም ቀጠና የመመሥረት እቅድ አላቸው።

ሆኖም ግን ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች ቀጠናው እንዳይፈጠር እንቅፋት ይሆናሉ።

ሰሜን ኮርያ ቀጣይ እርምጃዋን ለመወሰን የአሜሪካን ምርጫ በአንክሮ እየተከታተለች እንደሆነ አገረ ገዢው ያስረዳሉ።

"በሕይወት ሳለሁ ሰሜን እና ደቡብ ኮርያ ተዋህደው አላይም። ውጥረቱን ለሁለት ሴት ልጆቼ ማውረስ ግን አልፈልግም" ይላሉ።

ኪም ጆንግ ኡን ወደ ድርድር ይመለሳሉ? ወይስ ድንበሩን እንደዘጉ ይዘልቃሉ? የሚለው ጥያቄ ገና መልስ አላገኘም።

ዓመቱን በጥሞና ያሳለፉት መሪው፤ በትዕይንቱ አማካይነት አጀንዳቸውን እንደሚያሳዩ ይጠበቃል።