ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰብዓዊ መብት፡ ታዋቂው ሱዳናዊ የፊልም ባለሙያ በእስር ቤት እንደተገረፈ ተናገረ
ታዋቂው ሱዳናዊ የፊልም ባለሙያና የአለም አቀፉ የኦስካር ሽልማት ዳኛው ሃጆጅ ኩካ በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ከሰሞኑም እንደተገረፈ ተናግሯል።
የአካባቢውን ደህንነት አደጋ ጥላችኋል እንዲሁም ረብሻችኋል በሚል ወንጀል ነው እሱን ጨምሮ ስድስት አርቲስቶች ባለፈው ሳምንት በካርቱም የሚገኘው ፍርድ ቤት የሁለት ወር እስር የፈረደባቸው።
ከዚህም በተጨማሪ 90 ዶላርም እንዲከፍሉ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
ጠበቃቸው ግን ክሱ ትርጉም አይሰጥም በሚል ተከራክሯል።
ከእስር ቤት ሆኖ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን ሬድዮ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረገው የፊልም ባለሙያው፣ ሃጆጅ በመጀመሪያ እስር ቤት እንደገባ ይዞታው መጥፎ እንደነበርና ሁለት ጊዜም እንደተገረፈ አስረድቷል።
የእስር ቤቱ ሁኔታ በጣም መጥፎ ከመሆኑ አንፃር የአልጋ እጥረትም ነበር ብሏል።
ነገር ግን በአለም አቀፍ ሁኔታ አርቲስቶቹ እንዲለቀቁ የሚል ጥሪና የትብብር ዘመቻ መከፈቱን ተከትሎ የእስር ሁኔታቸው እንደተሻሻለና ስልክም ማግኘት እንደቻለ አስረድቷል።
ሆኖም መታሰራቸውን "በጣም ተስፋ አስቆራጭና አሳዛኝ" ያለው ሲሆን በህዝብ አብዮት ከስልጣን የተገረሰሱት የፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ስርአትም በተወሰነ መልኩ እንዳለ ማሳያ ነው ብሏል።
ለእስር የበቁት ነሐሴ ወር ላይ ሲሆን የአንድ ቲያትር ልምምድ ሲጨርሱ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ነው።
ፖሊስ በአካባቢው ደርሶ በቁጥጥር ስር ባዋላቸውም ወቅት እየዘፈኑና እየዘመሩ አካባቢውን ረብሸውታል የሚልም ክስ ቀርቦባቸዋል።
ጥቃት የፈፀሙት ግለሰቦች ግን በቁጥጥር ስር አልዋሉም።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በበኩላቸው የሱዳን የፍትህ ስርአትም ሆነ ፖሊስ አሁንም ቢሆን ከቀድሞው ስርአት ነፃ አለመሆኑን እየተናገሩ ነው።
የመናገርና የማሰብ ነፃነትን የሚከለክሉ ጨቋኝ የሚባሉ ህጎችም አሁንም ተግባራዊ እየሆኑ እንዳሉም እስሩ ማሳያም ነው ተብሎም እየተተቸ ነው።