የናይል ወንዝ በሱዳን ፒራሚዶች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተሰግቷል

ታትሟል

የናይል ወንዝ ገደቡን ጥሶ አብዛኛውን ካርቱምን አጥለቅልቋል። የሱዳን ጥንታዊ ቅርሶች ላይም ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት ሰፍኗል።

የአገሪቱ ባለስልጣናትም ጎርፍ ጥንታዊ ፒራሚዶች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ጥረት እያደረጉ ነው።

በአሸዋ በተሞሉ ከረጢቶች ጎርፉን ለመከላከል ጥረት እተደረገ ስለመሆኑ እና የጎርፍ ውሃ ከተኛባቸው ስፍራዎች ደግሞ በውሃ መሳቢያ የውሃ መጠን ለመቀነስ ሙከራ እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።

ሱዳን ከ2 ሺህ 300 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ፒራሚዶች መገኛ ነች።

ይህ በክፍለ ዘመን ከተከሰቱ ጎርፎች ከፍተኛ እንደሆነ የተነገረው መጥለቅለቅ በመሬት ውስጥ ተቀብረው የሚገኙ ቅርሶችን እንዳይጎዳም ተሰግቷል።

አልባጃዊያ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ስፍራ ሲሆን በሜሮ ጥንታዊ ሥልጣኔ ጊዜ የተገነቡ ፒራሚዶችን የያዘ ስፍራ ነው።

መንግሥት ጎርፉን ተከትሎ የ3 ወራት አስቸኳይ ጊዜን አውጇል።

ከመቶ ሰዎች በላይ ሞተዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ጎርፉ ግማሽ ካርቱምን ያጥለቀለቀ ሲሆን የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዱክ መኖሪያ ቤትም አላመለጠም።