የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የክረምቱ ዝናብ አሁንም የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቀቀ

ታትሟል

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የክረምቱ ዝናብ አሁንም የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቀቀ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አየር ትንበያ ዋና ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ጫሊ ደበሌ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የክረምት ዝናብ በቀጣዮች ቀናትም የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በአርሲና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች ዘጠኝ ወረዳዎችና 42 ቀበሌዎች ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።

በአፋር ክልል በሚገኙ 14 ወረዳዎች ደግሞ በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተነሳ ከ120 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የክልሉ የአደጋ መከላከል ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ኃላፊ አቶ ማሂ አሊ በተለይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ ማሂ አክለውም ቢያንስ 72 ሺህ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ እስከ ዛሬ ድረስ 43 ሺህ 670 ሰዎች በጎርፍ ምክንያት መፈናቀላቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ድረስ የጣለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የተነሳ 170 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ጉዳት ሲደርስባቸው 130 ሺህ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር ለቢቢሲ መግለፃቸው ይታወሳል።

የኦሮሚያ የአደጋ ስጋት ኮሚሽነር አባድር አብዳ በዚሁ ጉዳይ ላይ ጠይቀናቸው እንደተናገሩት የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ሰዎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉንና ንብረት ማውደሙን ገልፀው " የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በመፍሰሱ በአርሲና በምስራቅ ዞኖች ዘጠኝ ወረዳዎች 42 ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ከ19 ሺህ 900 በላይ ሰዎች ጎድቷል" ብለዋል።

በተጨማሪም በቤቶችና በደረሱ ሰብል ማሳዎች ላይ ጎርፉ ጉዳት ማድረሱን ገልፀዋል።

ለተጎዱት ሰዎች የምግብ እህል፣ አልባሳት ድጋፍ እየተሰጣቸው መሆኑን አንስተዋል።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት ሰዎች ሌላ ስፍራ እንደሰፈሩና ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ ዘመዶቻቸው በመሄድ እንደተጠለሉ ተናግረዋል።

"አንዳንድ ሰዎች በውሃ በተከበቡባቸው አካባቢዎች በትራክተርና፣ በጀልባ በመታገዝ አውጥተናል" ሲሉ ገልፀዋል።

አሁን በውሃ ተከብቦ እየተቸገሩ ያሉ አለመኖራቸውን የደረሰው አደጋ ከአቅም በላይ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በፈንታሌ ወረዳ መተሃራ ከተማ ከአንድ ቀበሌ የተፈናቀሉት ሰዎች የምግብ እህልና እንደ ምንጣፍ ያሉ ድጋፎች መሰጠት መጀመራቸውን አንስተዋል።

ሐሙስ ዕለት ከ3000 ፍራሽ በላይ 71 ኩንታል እህል፣ 170 ኩንታል ሩዝ እና ወተት ጭምር መሰጠቱን ተናግረዋል።

ሞልቶ የፈሰሰው ውሃ ከቅርብ ቀናት ወዲህ እየቀነሰ እንዳለ አንስተው በሚቀጥሉት ሳምንታትም በተከታታይ እየቀነሰ ከሄደ ሰዎች ወደ ቀያቸው ሊመለሱ ይችላሉ ብለዋል።

አሁንም ጎርፉ በቀነሰበት አካባቢዎች ሰዎች ወደቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን ይናገራሉ።

መተሃራ

የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ የተበጀለትን ቦይ በማፍረስ የምስራቅ ሸዋ ዞን ከተሞች ወደ ሆኑት ወንጂና መተሃራ ከተሞች ላይ ጉዳትን አድርሷል። በመተሃራ ከረቡዕ ማታ ጀምሮ በከተማዋ ካሉት ሁለት ቀበሌዎች አንዱ ሙሉ በሙሉ በጎርፍ ተጥለቅልቋል።

የከተማዋ ከንቲባ አቶ ታደለ ድሪብሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በመተሃራ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በከተማዋ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም ብለዋል።

"የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ወደ ከተማችን ፈስሷል ይህ ደግሞ በዚህ ከተማ ታሪክ ትልቅ አደጋ ነው። "

የደረሰው አደጋ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች በህይወታቸው ከመውጣት ውጪ ንብረታቸውን ሙሉ በሙሉ ማውጣት ሳይችሉ በመቅረታቸው እንደወደመባቸው ተናግረዋል።

ይህ ጎርፍ ሁለቱን ቀበሌዎች የሚያገናኘው መንገድ እንዲሁም ከምዕራብ ሃረርጌ ዞን ሃንቸር ወረዳ ጋር የሚያገናኘውን መንገድ ሙሉ በሙሉ በመቁረጡ ሰዎችን የማውጣት ስራ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል ሲሉ ከንቲባው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህም የተነሳ ከተማዋ ለሁለት ተከፍላ እንደምትገኝም ይገልጻሉ።

አሳይታ አፋምቦ ዱብቲ እና ቀጠና 3 የሚባሉ አካባቢዎች ደግሞ የተጎዱ ሰዎች ከፌደራል፣ ከክልል መንግሥት እንዲሁም ከእርዳታ ድርጅቶች የምግብ እህልና ቁሳቁሶች ድጋፍ እየቀረበላቸው መሆኑን ሰምተናል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አየር ትንበያ ዋና ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ጫሊ "አሁንም ቢሆን፣ በመካከለኛ ፣ ምዕራብ እና ምስራቅ አገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም ደጋማ የደቡብ ክፍል ከፍተኛ ዝናብ ይጠበቃል" ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የሚዘንበው ዝናብ አፈሩ ውሃ መጥገቡ በቀላሉ ጎርፍ ማስከተል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሯ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ወ/ሮ ጫሊ እንዳሉት ከዚህ በፊትም በሰኔ ወር ውስጥ ከፍተኛ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስቀድሞ ማስጠንቀቁን ተናግረዋል።

በግንቦት ወር ውስጥም ከትልቁ ፓስፊክ ውቅያኖስ በሚመጣው የንፋስ እንቅስቃሴ ላይ በመመስረት የአየሩን ሁናቴ መተንበይ የሚያስችል መረጃ ሲያሰባስቡ እንደቆዩ አብራርተዋል።

በተጨማሪም አደጋው ባስከተለው አዋሽ ወንዝ አካባቢ የመኸር እና ክረምት ወቅቶች ጎርፍ የሚያስከትል ዝናብ እንደሚኖርና የአፈር እርጥበት እንደሚከሰት መተንበያቸውን ጠቅሰዋል።

ዘንድሮም ክረምት ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች በአንዳንድ ስፍራዎች መደበኛውን መጠን የሚያገኙ ቢሆንም አንዳንዶች ደግሞ ከሚጠበቀው በላይ ማግኘታቸውን ዳይሬክተሯ ገልፀዋል።

በሐምሌ ወቅት ዝናብ በተከታታይ በመዝነቡ፣ በነሐሴ ወር ደግሞ ከፍተኛ ዝናብ መኖር ለተከሰተው ጎርፍ አስተዋጽኦ ማድረጉን አንስተዋል።