የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በብራዚል በፍጥነት እንዴት ተስፋፋ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት መካከል አንዷ ብራዚል ናት። ወረርሽኙ ከተከሰተበት መጋቢት ወር አንስቶ ከ2 ሚሊየን ሰዎች በላይ በቫይረሱ ተይዘዋል።
እንደ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ አጠቃላይ ቁጥሩ 2 ሚሊየን 12 ሺህ 151 ነው። በዚህም ከአሜሪካ በመቀጠል በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቃች ሁለተኛዋ የዓለማችን አገር ሆናለች።
በቫይረሱ ሳቢያም ከ74 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። በቂ ምርመራ ስላልተደረገ እንጂ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ይታመናል።
ለመሆኑ ቫይረሱ በደቡብ አሜሪካ አገራት እንዴት በፍጥነት ሊዛመት ቻለ?
ወረርሽኙ በተከሰተበት ጊዜ ብራዚል ለመድረስ ጊዜ ወስዶ ነበር። በመጀመሪያው ዙር የቫይረሱ ስርጭት ክፉኛ የተጎዱት የአማዞን አካባቢዎች ነበሩ።
በአካባቢውም በወረርሽኙ በርካታ ሰዎች በመቀጠፋቸው ባለሥልጣናት በአካባቢው ያለው የአስክሬን ሳጥኖች ሊያልቁ እንደሚችሉ ሲያስጠነቅቁ ነበር።
ከዚህም ባሻገር ሰፊ የመቃብር ቦታዎች እንዲያዘጋጁም ተገደዋል።
በአካባቢው የአገሬው ነባር ማህበረሰቦች በቫይረሱ ክፉኛ ተጠቅተዋል። የአብዛኞቹ መኖሪያ ቤቶች የሚገኙት ከጤና ተቋማት ርቀው በመሆኑ በቶሎ ህክምና ማግኘት አልቻሉም።
በጎ ፍቃደኛ ነርሶችም ወደ ስፍራው በማቅናት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ጥረት አድርገዋል።
ምንም እንኳን በቫይረሱ የሚያዙም ሰዎች ቁጥር ቢጨምርም አገሪቷ የእንቅስቃሴ ገደብ አልጣለችም።
ቤት ውስጥ የመቀመት ገደቡም ቢሆን በፕሬዚደንት ጄር ቦልሶናሮ ተተችቷል። ከዚህም ባለፈ ቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደቦችን ለመቃወም በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ተገኝተዋል።
ፕሬዚደንቱ ቫይረሱን "ቀላል ጉንፋን" በማለት ሲያጣጥሉት የነበረ ሲሆን፤ ለወረርሽኙ በሰጡት ምላሽም በከፍተኛ ሁኔታ ተተችተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉም ከቫይረሱ በባሰ ጉዳት ያስከትላል ያሉት ፕሬዝድንቱ በሕብረተሰቡ ዘንድ 'ጭንቀት' ለመፍጠር በሚያሰራጩት መረጃ መገናኛ ብዙሃንን ከሰዋል።
ፕሬዚደንቱ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉም ከደጋፊዎቻቸው ጋር ይገናኙ ነበር።
ምንም እንኳን በርካቶች የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ በኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ያስከትላል ሲሉ ቢቃወሙትም የጤና ባለሥልጣናት ግን በሃሳቡ አይስማሙም።
በዚህ የተነሳ ሁለት የጤና ሚኒስተር የነበሩ ዶክተሮችም፤ አንዱ በመባረራቸው ሌላኛ በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀዋል።
ታዲያ ፕሬዚደንቱ 'ቀላል ጉንፋን' ሲሉ ባጣጣሉት ቫይረስ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በዚሁ ቫይረስ ተይዘዋል።
በአገሪቷ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቢጨምርም የእንቅስቃሴ ገደቦች ተነስተዋል።
ሆኖም ሁለት የክትባት ሙከራዎች ተስፋ ሰጥተዋል። ክትባቶቹ በቅርቡ በሺዎች በሚቆጠሩ ብራዚላዊያን በጎ ፈቃደኞች ላይ የመጨረሻ ሙከራ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።












