የኮሮናን ህግ ተላልፈዋል የተባሉት ህንዳዊው የእስልምና እምነት ምሁርና ሰባኪ "በግድያ" ወንጀል ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Hindustan Times
ህንዳዊው የእስልምና እምነት ምሁርና ሰባኪ መሃመድ ሳድ ካንዳቪ አገሪቷ ያሳለፈችውን አስገዳጅ ቤት የመቀመጥ ውሳኔ በመተላለፋቸው "በግድያ "ወንጀል ተከሰዋል።
ሰባኪው የወረርሽኙ ማዕከል በሆነችው ደልሂ ስብሰባ አካሂደዋል በሚል ነው የተከሰሱት።
ፖሊስ እንዳሳወቀው ኒዛሙዲን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው መስጊድ የተጀመረው ስብሰባ ባለፈው ወር ህንድ ቤት የመቀመጥ ውሳኔን ከማወጇ በፊት የተጀመረ ቢሆንም፤ ውሳኔውም ተግባራዊ ከሆነ በኋላም ህጉን ተላልፈው በስብሰባው ቀጥለዋል ብሏል።
ስብሰባው በአስራ ሰባት ግዛቶች ውሰጥ ከተጠቁት 1023 የኮሮና ቫይረስ ህሙማን ጋር ቀጥታ ግንኙነት አለው የተባለ ሲሆን፣ ከሌላ አገር በመጡ በስብሰባው ተሳታፊዎች ነው ቫይረሱ የተዛመተው ተብሏል።
ሰባኪውም ሆነ ድርጅታቸው ምንም ስህተት አልፈፀምንም በማለት የፖሊስን ውንጀላ አጣጥለውታል።
የዴልሂ ፖሊስ በበኩሉ መሃመድ ሳድ የሰዎችን ህይወት አደጋ በመጣልና፣ ለሞት በመዳረግ እንደተከሰሱና የዋስ መብታቸው እንደማይከበር አስታውቋል።
ሰባኪው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ሲሆን፣ በሌሉበትም ክሳቸው ቀርቧል።
ፖሊስ አክሎም ሁለት ጊዜ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ውስጥ የነበረውን ስብሰባ ቀጥለውበታል በማለት ተናግሯል።
ድርጅታቸው ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬድራ ሞዲ አስገዳጅ የቤት መቀመጥ መመሪያ ሲሰማ ስብሰባው እንደተቋረጠና ተሳታፊዎችም ወደየቤታቸው እንዲሄዱ መወሰኑን አሳውቀዋል።
ምንም እንኳን ብዙዎች ወደመጡበት ቢመለሱም፣ ከተሞች ድንበሮቻቸውን መዝጋታቸውን ተከትሎ አንዳንዶች ወደ አካባቢያቸው መመለስ አልቻሉም።
ህንድ በከተሞች ያሉ ድንበሮችን ከመዝጋት በተጨማሪ የአውቶብስና ባቡሮች እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥላለች።
በዚህም የተነሳ በመስጊዱ ውስጥ ባሉ ማደሪያዎች ተሳታፊዎቹ ሊቆዩ ተገደዋል። ማደሪያዎቹ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎችንም ማስተናገድ ይችላሉ ተብሏል።
አዘጋጆቹ ጨምረውም በአካባቢው ለሚገኙ ፖሊሶች እንዳሳወቁና የጤና ባለሙያዎችም በግቢው በመገኘት ተሳታፊዎቹን ሲመርመሩም ሆነ ሁኔታውን ሲቆጣጠሩ እንደተባበሩ አስረድተዋል።














