ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዓለም ባንክ ለኮሮናቫይረስ ድንገተኛ እርዳታ 12 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገባ
የዓለም ባንክ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ትግል ውስጥ ያሉ አዳጊ አገራትን ያግዝ ዘንድ የ12 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብቷል።
ዓለም ባንክ ገንዘቡን የሚሰጠው በብድር፣ በእርዳታና በቴክኒክ ድጋፍ መልክ ሲሆን ባንኩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የዓለም መሪዎች ኮሮናቫይረስ ኢኮኖሚያቸውን እንዳያሽመደምድ ብርቱ ዝግጅት ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ነው።
ኮሮናቫይረስ ኢኮኖሚዎች ላይ የሚያስከትለው መቀዛቀዝ አገራትን ችግር ውስጥ ሊከት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
ይህ የዓለም ባንክ እርዳታ አገራት የኮሮናቫይረስን ስርጭት በመከላከል ረገድ የጤና አገልግሎት ስርዓቶቻቸውን እንዲያጠናክሩና ቫይረሱ የሚያሳድረውን ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ለመቀነስ ከግል ዘርፍ ጋር እንዲሰሩ ለማስቻል ነው።
"ለማድረግ እየሞከርን ያለነው የቫይረሱ ስርጭት እንዲገታ ነው" ብለዋል የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ።
ዓለም ባንክ እንዳስታወቀው እርዳታውን በቅድሚያ የሚሰጠው በጣም ድሃ ለሆኑ አገራትና ለቫይረሱ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ለሆኑ አገሮች ነው።
ኮሮናቫይረስ በ70 አገራት ላይ እንደተሰራጨ የሚታወቅ ነው።
ዓለም ባንክ ቃል የገባው ገንዘብ ግማሽ ያህሉ ከባንኩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ኮርፖሬሽን የሚገኝ ሲሆን አራት ቢሊዮን የሚሆነው ደግሞ ቀደም ሲል ከነበሩ ፈንዶች ተዘዋውሮ የሚመጣ እንደሆነ ተገልጿል።
እስካሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ 92 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን 80 ሺህ የሚሆኑት ኬዞዎች የተመዘገቡት ቻይና ውስጥ ነው። በሌላ በኩል ሶስት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ የሞቱ ሲሆን በተመሳሳይ ብዙዎቹ ሞቶች የተመዘገቡት በቻይና ነው።
በዛሬው እለት 38 ሞቶች በቻይና የተመዘቡ ቢሆንም የቻይና መንግሥት እንቅስቃሴን የሚገቱ ጥብቅ እገዳዎችን በመጣሉ ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ አዳዲስ በኮሮናቫይረስ የመያዝ ሪፖርቶች ቀንሰዋል እየተባለ ነው።