አሜሪካ፡ የ10 ዓመቱ ሕጻን ሞግዚቱ በስህተት በተኮሰችው ጥይት ተመታ

ሽጉጥና ትይት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዘንድሮ በአሜሪካ ብቻ 6ሺህ 155 ሰዎች በጥይት ተመትተው ሞተዋል
ታትሟል

አሜሪካ ሂውስተን ውስጥ ሞግዚቷ ቤት ውስጥ የተቀመጠ ሽጉጥ በማንሳት ሰልፊ መነሳት ትፈልጋለች። ነገር ግን ያሰበችውንም ፎቶ ሳትነሳ በአደራ የተሰጣትን ልጅ ተኩሳ ማቁሰሏ ተሰምቷል።

ካትሊን ስሚዝ ልጁን ሆዱ ላይ ተኩሳ የመታችው ማክሰኞ ዕለት ሲሆን ሽጉጡ ጥይት መጉረሱን አታውቅም ነበር ተብሏል።

ሞግዚቷ የልጁ አክስት መሆኗ የተነገረ ሲሆን ዕድሜዋም 19 ነው።

ህፃንን ልጅ በመጉዳትና ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ ወንጀል ተከስሳለች።

ሕጻኑ በከፋ የጤንነት ሁኔታ ላየ የሚገኝ ቢሆንም ያገግማል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

እንደ ፎክስ 26 ዘገባ ከሆነ ልጁን የመታው ጥይት ወሳኝ የአካል ክፍሎቹን አላገኘውም።

የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ እንደተናገሩት መሳሪያው የተቀመጠበት ስፍራ በቀላሉ የሚገኝና ለእይታ የተጋለጠ ነበር።

አክለውም "ልጅቱ ሽጉጡን ያነሳችው ፎቶ ለመነሳት እንደነበር ገልጻለች። በዚህ መካከል ሽጉጡ ባርቆ ልጁን አንደመታው ለማወቅ ተችሏል።" ካሉ በኋላ "... በጣም አሳዛኝ ነገር ነው፤ እንዲህ አይነት ነገር አንዳንዴ ይገጥመናል" ብለዋል።

ቶማስ ጊሊላን ከፍተኛ የፖሊስ ኃላፊ ሲሆኑ ለሲኤኤን በሰጡት ቃል " የጦር መሳሪያዎች አደገኞች ናቸው፤ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳይከሰት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል። ሽጉጥ ይዞ ሰልፊ መነሳት ደግሞ የሚመከር አይደለም" ብለዋል።

ዘንድሮ በአሜሪካ ብቻ 6ሺህ 155 ሰዎች በጥይት ተመትተው ሞተዋል።

ከእነዚህ ሞቶች መካከል 321 ሳይታሰብ የተከሰተ ነው።

ባለፈው ዓመት ብቻ 3,760 እድሜያቸው ከ18 በታች የሆኑ ሕፃናት በጥይት ተመትተው ሞተዋል።