"ማማውን ከ10 ዓመት በላይ ሰርቼዋለሁ"፡ ጎንደር ላይ አደጋ ያጋጠመውን ማማ የሰራው አናጺ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የጥምቀት በዓል በጎንደር ሲከበር በተለይ እንግዶች ባሕረ-ጥምቀቱን የተሻለ ቦታ ሆነው እንዲያዩ በማሰብ ለዓመታት የእንጨት ማማ እየተሰራ እዚያ ላይ እንዲቀመጡ ይደረጋል።
በተመሳሳይ ዘንድሮም የእንግዳው ቁጥር ሊጨምር ይችላል በሚል እሳቤ ከአሁን በፊት ከነበረችው አንዲት ማማ በተጨማሪ ሦስት ማማዎች መሰራታቸውን የጎንደር ከተማ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ ተናግረዋል።
ማማው የተሰራው ከአሁን በፊት ሲሰራው በነበረው አናጺ መሆኑን የተናገሩት አቶ አስቻለው የተሰራውም ከዚህ በፊት በተሰራበት የእንጨት መጠን ነው ይላሉ።
"ከዚህ በፊትም እንግዶችን ለማስቀመጥ ሲባል ተመሳሳይ ማማ በመሥራት እንደግዶችን እናስተናግድ ነበር፤ ዘንድሮ አደጋ ያጋጠመው ማማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ማማው ላይ ስለወጣበት ነው" ይላሉ።
ሰዉ ማማው ላይ በፊት ለፊት በኩል ለመውጣት ሲሞክር በጥበቃዎች በመከልከሉ ከኋላ በኩል ብዙ ሰው ተንጠላጥሎ ስለወጣበት ሚዛኑን ስቶ መውደቁን ያብራራሉ።
ማማውን የሰራው አናጺ አቶ ወንድም በቀለ ይባላል። እርሱ እንደሚለው በዚሁ በአጼ ፋሲል የመዋኛ ገንዳ ለጥምቀት በዓል ማድመቂያ እየተባለ ላለፉት አስር ዓመታት ማማውን ሲሰራ ቆይቷል።
በሥራውም ተመሳሳይ ዲዛይን እንደሚጠቀም የተናገረው አናጺው "የዘንድሮውን ማማ የሠራሁት አምና በሰራሁበት እንጨት ልክ ነው" ብሏል።
በአብዛኛው ከአሁን በፊት ዘንድሮ የተሰራውን ማማ ለሚቀጥለው ዓመት የተጎዳውን እንጨት በመቀየር ሲሰራ እንደቆየም ተናግሯል።
ዘንድሮ ከተጨመሩት ሦስት ማማዎች መካከል አንዷን የሰራት ወንድም ነው። ባለፈው ዓመት ተሰርታ ዘንድሮም ጥቅም ላይ የዋለችውን ማማም የሰራው ወንድም ነው።
ወንድም እንደሚለው እርሱ አምና የሰራት እና ሌሎች ጓደኞቹ ዘንድሮ የሰሯቸው ሁለት ማማዎች በድምሩ ሦስት ማማዎች ለእንግዶች የተዘጋጁ ስለነበሩ በልካቸው ብቻ ሰው እንዲይዙ ተደርገው ምንም ጉዳት አላደረሱም።
ነገር ግን አንዷ እርሱ ዘንድሮ የሰራት ማማ ለሕዝቡ የተሰራች ስለነበረችና ሕዝቡም ያለገደብ ስለተሰቀለባት አደጋውን ለማስተናገድ ተገድዳለች ይላል።
"በፊት ለፊት በኩል ያለውን መከላከያ እየጠበቀው ስለነበር በአብዛኛው ከኋላ የመጡ ሰዎች ናቸው መጥተው የሰፈሩበት። እዚያ ላይ የቆሙት የጥበቃ ሰዎች ማስቆም ነበረባቸው። ምክንያቱም የሌሎቹ መቀመጫዎች ይበቃል ተብሎ በልካቸው ብቻ ሰው ስለተቀመጠ ምንም የደረሰባቸው ነገር የለም። ነገር ግን ይሄኛው ከኋላ የመጣ ሰው ስለወጣበት ውረዱ ሲባሉም የሚሰማ በመጥፋቱ ሚዛኑን ስቶ ተደርምሷል"
"እስካሁን ከሰራሁት በተለየ መልኩ ዘንድሮ የተሻለ አድርጌ ነው የሰራሁት፣ በተደጋጋሚ አረጋግጨዋለሁ" በማለት የሰራው ማማ ጥራቱን የጠበቀ እንደነበር አናጺው ይናገራል።
የጎንደር ከተማ የሰላም ግንባታና የሕዝብ ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋ መኮንን በበኩላቸው የአደጋው ምክንያት የጥራት ማነስ ይሁን አይሁን ወደፊት በባለሙያ ተጣርቶ የሚገለጽ እንጂ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዲህ ነው ለማለት አልችልም ብለዋል።
በአደጋው የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የሟቾችን ቁጥር በተለያየ አሃዝ ገልጸውታል። አቶ ተስፋ በአደጋው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 10 መሆናቸውን እና ከእነዚህም መካከል 3ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተረጋግጠዋል።
እንደ አቶ ተስፋ ገለጻ በአደጋው 147 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተልከዋል። ከነዚህ መካከል 67 የሚሆኑት ወዲያውኑ ታክመው ወደቤታቸው ተመልሰዋል።
80 የሚሆኑት ደግሞ እስካሁን ሆስፒታል ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው ነው። ከነዚህ መካከል 2 ተጎጅዎች በጣም የከፋ አደጋ ውስጥ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ተስፋ የተወሰኑ የውጭ ዜጎችም ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።












