ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢራን ብቸኛዋ ሴት የኦለምፒክ ሜዳሊያ ባለቤት ሃገር ጥላ መሸሿን አሳወቀች
የኢራን ብቸኛዋ ሴት የኦለምፒክ ሜዳሊያ ባለቤት ኪሚያ አሊዛዴህ ሃገር ጥላ እንደሸሸች አሳወቀች።
የ21 ዓመቷ አሊዛዴህ በማሕበራዊ ድር-አምባ ገጿ ይፋ እንዳደረገችው፤ 'ሃገሬን ጥዬ የሸሸሁት በዋናነት ኢራን ውስጥ ያለው ግብዝነት፣ ውሽትና ኢ-ፍትሃዊነት አካል መሆን ባለመፈለጌ ነው' ብላለች።
አሊዛዴህ ራሷን ኢራን ውስጥ ከሚገኝ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጨቋኝ ሴቶች አንዷ ስትል ትገልፃለች።
አሊዛዴህ ያለችበትን ሥፍራ በይፋ ባታሳውቅም ኔዘርላንድስ ውስጥ ልምምድ ታደርግ እንደነበር ተነግሯል።
2016 ብራዚል በተካሄደው የሪዮ ኦለምፒክ ላይ በቴኳዋንዶ የስፖርት ዓይነት ብር በማምጣት ታሪክ ሠርታለች። ነገር ግን የኢራን ባለሥልጣናት ድሌን ለፕሮፖጋንዳቸው ተጠቅመውባታል ስትል በማሕበራዊ ገጿ መልዕክት ላይ አስፍራለች።
ኢራን፤ በስህተት የዩክሬን አውሮፕላንን መትቼ ጥያለሁ ብላ ካመነች በኋላ ይህ ያበሳጫቸው ኢራናውያን አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ማሰማት በጀመሩበት ወቅት ነው አሊዛዴህ ሃገር ጥላ መሸሿን ያሳወቀችው።
«ልበሽ ያሉኝን ለብሻለሁ፤ በይ ያሉኝን ብያለሁ። እያንዳንዷን ቃል አነብንብያለሁ። እኛ ማለት ለእነሱ [ለኢራን ባለሥጣናት] ግዑዝ ነን።»
ምንም እንኳ መንግሥት የሷን ድል ለፕሮፖጋንዳ ቢያውለውም ባለሥልጣናቱ 'ሴት ልጅ እግሯን ማንሳት የለባትም' በማለት ያንጓጥጧት እንደነበር ይፋ አድርጋለች።
አሊዛዴህ ወደ የትኛው ሃገር እንደሸሸች ይፋ ማድረግ አልፈቀደችም፤ አውሮጳ ናት ተብሎ የተነገረውንም አስተባብላለች።
የኢራናውያን የአሊዛዴህን መሸሽ ሲሰሙ መደናገጣቸው አልቀረም። ፖለቲከኛው አብዶልካሪም ሆሴንዛዴህ 'አቅም የሌላቸው ፖለቲከኞች የሰው ኃይል እንዲሸሽ እያደረጉ ነው' ሲል ወቀሳውን አሰምቷል።
አሊዛዴህ ቶክዮ በሚካሄደው ኦለምፒክ ላይ እንደምትሳተፍ ይጠበቃል። የኢራንን ባንዲራ ማውለብለቧ ግን እርግጥ አልሆነም።
ሃገር ጥላ የሸሸችው አሊዛዴህ ስለ ወደፊት ዕቅዷ ምንም ያለችው ነገር ባይኖርም 'ሁልጊዜም የኢራን ልጅ ነኝ' ስትል መልዕክቷን ቋጭታለች።