ቤንጃሚን ኔታንያሁ ለቀረበባቸው ክስ ያለመከሰስ መብቴ ይከበርልኝ ሲሉ ጠየቁ

ታትሟል

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከቀረበባቸው የሙስና ክስ ጋር በተያያዘ ያለመከሰስ መብቴ ይከበርልኝ ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን ጠየቁ።

ውሳኔው ቀጣዩ ምርጫ እስከሚካሄድበት መጋቢት ወር ድረስ ፋታ ይሰጣቸው ይሆናል ተብሏል።

ባለፈው ሕዳር ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በጠቅላይ አቃቤ ሕጉ የበላይ ኃላፊ በጉቦ፣ ማጭበርበርና እምነት ማጉደል በሶስት የተለያዩ ክሶች ተከሰው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ምንም ጥፋት አልሰራሁም በማለት ሁሉንም ክስ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን የያለመከሰስ መብታቸው እንዲከበርላቸው የሕዝብ እንደራሴዎቹን ከግማሽ በላይ ሊደግፏቸው ይገባል።

ኔታንያሁ እስራኤልን ለረዥም ጊዜ ያስተዳደሩ መሪ ሲሆኑ፣ የቀረበባቸው ክስ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ በሀብት ከናጠጡ ነጋዴዎች ስጦታ ተቀብለዋል፣ በመገናኛ ብዙኅን በጎ ገጽታ ተላብሰው ለመታየትም ያላግባብ ውለታ ገብተዋል የሚል ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌዢዥን ቀርበው የሕዝብ እንደራሴዎችን ያለመከሰስ መብታቸው እንዲከበርላቸው የጠየቁት መጠየቂያ ጊዜው ከማብቃቱ ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብለው ነበር።

በንግግራቸውም "ይህ ጥያቄዬ ሕጉን የተከተለ ነው...ዓላማውም እናንተን ለማገልገል፣ ለእስራኤል መጻዒ እድል በማሰብ ነው" ብለዋል።

ቤንጃሚን ኔታንያሁ በመጪው መጋቢት ወር ለሶስተኛ ጊዜ ለብሔራዊ ምርጫ ይቀርባሉ።

በእስራኤል ሕግ መሰረት አንድ ጊዜ የያለመከሰስ መብት ከተጠየቀና ምርጫ ከመደረጉ በፊት ምክር ቤቱ ከተበተነ ክሱ ችሎት ቀርቦ አይታይም።

በእስራኤል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከአቃቤ ሕግ በቀጥታ ያለመከሰስ መብታቸውን ማግኘት የማይችሉ ሲሆን ነገር ግን አስፈላጊ በሆነ ሰዓት ሁሉ መጠየቅ ይችላሉ።

በስልጣን ላይ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣን እንዲወርድ የሚደረገው ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘና ከተፈረደበት ብቻ ነው።

ቤንጃሚን ኔታንያሁ ክሱን "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ" ብለውት የነበረ ሲሆን፤ "የውሸት ክስ እንዲያሸንፍ አልፈቅድም" ብለው ተናግረው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀናቃኝ የሆኑ ፖለቲከኞች ያለመከሰስ መብቴ ይከበርልኝ ብለው በመጠየቃቸው ተበሳጭተዋል።

ኔታንያሁ የተከሰሰሱት በምንድን ነው?

አቃቤ ሕግ ማንደልብሊት እንዳሉት፤ ኔታንያሁን በሦስት የተለያዩ ጉዳዮች ክስ ያቀርቡባቸዋል። ክሶቹ፤ ኬዝ 1,000፣ ኬዝ 2,000 እና ኬዝ 4,000 ይሰኛሉ።

  • ኬዝ 1,000ኔታንያሁ በማጭበርበር እና እምነት በማጉደል ተከሰዋል። ከሀብታም ወዳጃቸው ሻምፓኝ፣ ሲጋራና ሌሎችም ውድ ስጦታዎች በጉቦ ተቀብለዋል ተብሏል። ኔታንያሁ ግን ስጦታዎቹ የወዳጅነት መግለጫ እንጂ ጉቦ አይደሉም ብለዋል። ጓደኛቸውም ምንም ስህተት አልተሠራም ብለዋል።
  • ኬዝ 2,000 በዚህ ላይም ኔታንያሁ በማጭበርበር እና እምነት በማጉደል ተከሰዋል። የዜና ሽፋን ለማግኘት ከጋዜጣ አሳታሚ ጋር ተዋውለዋል ተብሏል። አሳታሚውም ክስ ተመስርቶበታል። ሆኖም ግን ኔታንያሁና አሳታሚው አንዳችም ስህተት አልሠራንም ብለዋል።
  • ኬዝ 4,000ይህ ከሁሉም ክሶች ከባዱ ነው። ኔታንያሁ በጉቦ፣ በማጭበርበር እና እምነት በማጉደል ተከሰዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ለዜና ሽፋን ሲሉ አውራ የቴሌኮም ድርጅትን የሚጠቅም ሕግ አስተዋውቀዋል ተብለዋል። ሕጉ በባለሙያዎች የተደገፈ እንደሆነ የገለጹት ኔታንያሁ ግን ከተቋሙ ምንም ጥቅም እንዳላገኙ ተናግረዋል። ድርጅቱም ምንም አለማጥፋቱን ገልጿል።