ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አየር መንገዶች ለምን ሆን ብለው የበረራ ሰዓት ያራዝማሉ?
የበረራ ሰዓቶች በጊዜ ሂደት እየተራዘሙ መምጣታቸውን አስተውለው ያውቃሉ?
ይህ አየር መንገዶች በመዳረሻ አየር ማረፊያ በሰዓታቸው ለመድረስ እየተጠቀሙት ያለው እየተለመደ የመጣ ስርዓት ነው። ተጓዦቻቸው ግን እንዲያውቁት አይሹም።
በ1960ዎቹ ከኒው ዮርክ - ሎስ አንጀለስ የሚደረገው በረራ ይፈጅ የነበረው 5 ሰዓት ሲሆን ዛሬ ላይ ግን ከኒው ዮርክ ተነስተው ሎስ አንጀለስ ለመድረስ ከስድስት ሰዓታት በላይ አየር ላይ መቆየትን ይጠይቃል።
ይህ የሆነው ሆን ተብሎ አየር መንገዶች የበረራ ሰዓታቸውን በመማራዘማቸው ነው። ለምን?
አየር መንገዶች በተደጋጋሚ በሚያጋጥማቸው የበረራ መዘግየት የሚባክነውን ጊዜ ለማካካስ የበረራ ሰዓታቸውን ያራዝማሉ። ከመነሻቸው የዘገዩ በረራዎች በመዳረሻቸው ላይ በተጠቀሰው ሰዓት ለመድረስ በማሰብ። ይህም የሚሆነው ለበረራ ቀድመው የሚሰጡት ረዘም ያለ የበረራ ሰዓት አማካኝነት ነው።
በሰዓታቸው የሚነሱም በረራዎች፤ በመዳረሻቸው ከማረፋቸው በፊት የተጠቀሰውን ሰዓት ያክል አየር ላይ ለመቆየት የሚገደዱበት ዕድል ሰፊ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
አንድ በረራ ቀድሞም ሆነ ዘግይቶ መድረሱ ብዙ ስርዓቶችን ያጨናግፋል። ለምሳሌ አየር ማረፊያው የማስተናገድ አቅም እንዲሁም አውሮፕላኑ መንገደኞችን የሚያራግፍበት በር የማግኘት ጉዳዮች ጥያቄ ውስጥ ይገባሉ።
ባጭሩ፤ አየር መንገዶች ከሚፈለገው በላይ ተጨማሪ ሰዓትን ይሰጣሉ።
አየር መንገዶች አገልግሎታቸውን ቀልጣፋ በማድረግ የመነሻ እና የመዳረሻቸውን ሰዓት ልከኛ ከማድረግ ይልቅ፣ ረዥም ሰዓትን በአየር ላይ መቆየትን እንደ አማራጭ መውሰዳቸው ዘርፈ ብዙ ችገሮችን እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የመጀመሪያው የመንገደኞች ጊዜ ይባክናል። ሁለተኛ ደግሞ አውሮፕላኖች ብዙ ሰዓትን አየር ላይ በቆዩ መጠን የሚለቁት ከፍተኛ መጠን ያለው የካርበን ልቀት በአየር ጸባይ ለውጥ ላይ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
የአቪዬሽን አማካሪው ኤቲኤች ግሩፕ ፕሬዝደንት የሆኑት ካፒቴን ማይክል ባኢዓዳ የአሜሪካን የትራንስፖርት ዲፓርትመንት ሪፖርትን ዋቢ በማድረግ፤ "በየቀኑ በአማካይ 30 በመቶ የሚሆኑ በረራዎች 15 ደቂቃዎችን እያረፈዱ በመዳረሻ ስፍራቸው ይደርሳሉ" ይላሉ።
ከዚህ ቀደም እያረፈዱ በመዳረሻቸው ይደርሱ የነበሩት የበረራዎች ቁጥር 40 በመቶ ነበር። አየር መንገዶች የበረራ ሰዓታቸውን ማራዘማቸውን ተከትሎ የአርፋጅ አውሮፕላኖች ቁጥር መቀነሱን ካፒቴን ማይክል ያስረዳሉ።
"አየር መንገዶች በስርዓቱ እየተጫወቱ ደንበኞች ላይ ይቀልዳሉ" ይላሉ።
የአሜሪካ የትራንስፖርት ዲፓርትመንት አንድ በረራ 'ዘግይቷል' የሚባለው አውሮፕላኑ ከ15 ደቂቃ በላይ ዘግይቶ በመዳረሻው ሲደርስ ነው ይላል።
አየር መንገዶች የበረራ ሰዓትን ባራዘሙ መጠን በከባባዊ አየር እና በተጓዞች ላይ የሚደርሰው ተጽእኖ ከፍ እያለ እንደሚመጣ ካፒቴን ማይክል ይናገራሉ። ታዲያ ለዚህ የሚሆነው መፍትሄ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን ማዘመን መሆኑን ይናገራሉ።