ጀርመናዊው ወንጀለኛ ከኢንተርኔት የመረሳት መብቱ እንዲከበርለት ፍርድ ቤት ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በግሪጎሪያን አቆጣጠር 1982 ላይ በፈፀመው የግድያ ወንጀል የ25 ዓመት አስራት ተፈርዶበት የነበረ አንድ ጀርመናዊ ስሙ ከኢንተርኔት መዛግብት ላይ እንዲፋቅ ፍርድ ቤት ወሰነለት።
ግለሰቡ ሁለት ሰዎችን አነስተኛ መርከብ ላይ እንዳሉ ገድሏል ተብሎ ነው የእስር ፍርዱ የተበየነበት።
ሰውዬው ከ20 ዓመት እሥር በኋላ የተለቀቀ ሲሆን የኔና የቤተሰቤ ስም ከሠራሁት ወንጀል ጋር ግንኙነት እንዳይኖረው በሚል ነው ለፍርድ አቤት ያለው።
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት የሰውየው ስም ከኢንተርኔት መዛግብት ላይ እንዲፋቅና መገናኛ ብዙሃንም ስለሰውየው መረጃ የመበርበር መብታቸው እንዲነጠቅ ወስኗል።
ግሰለቡ፤ የካሬቢያን ደሴት የሆነችው አፖሎኛ ላይ ሳለ ሁለት ሰዎችን በጥይት መቶ ገድሏል፤ እንዲሁም አንድ ተጨማሪ ሰው አቁስሏል።
ይህ ድርጊቱን በተመለከተ ዘጋቢ ፊልም ተሠርቶበታል፤ መፅሐፍም ተፅፏል።
አንድ የጀርመን ጋዜጣም ስለሰውየው የሠራቸውን ዘገባዎች ድረ-ገፁ ላይ ጭኗል። ማንኛውም ሰው ጉግል ላይ ገብቶ ቢፈልግ የሚያገኛቸው መረጃዎች ናቸው።
ይህ ጉዳይ ሰላም የነሳው ግለሰብ 'ራሴን ቀይሬ ጠቃሚ ዜጋ የመሆን መብቴን' ነጥቀውኛል ሲል ለፍርድ ቤት ከሷል።
የፌዴራሉ ፍርድ ቤት የሰውየው ግለሰባዊ መብት ከሕዝባዊ ጥቅምና ከፕሬስ ነፃነት አይበልጥም ብሎ ቢሽረውም የጀርመን ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት የሰውየው መብት ሊከበር ይገባል ሲል ፈርዷል።
ፍርዱ ወደ ፌዴራል ፍርድ ቤት ወርዶ የሚፀና ከሆነ የሰውየው መረጃዎች ሙሉ በሙሉ ከኢንተርኔት መዛግብት ይፋቃሉ።
'የመረሳት መብት' በተለይ አወሮጳ ውስጥ አከራካሪ ጉዳይ ሲሆን በአውሮጳ ሕብረትና በጉግል መካከል ቅራኔ እየፈጠረም ይገኛል።













