ሲድኒ መጠጥ ቤቶች ላይ የጣለችውን ሰዓት እላፊ አነሳች

ተቃውሟቸውን ያሰሙ ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የአውስትራሊያዋ ሲድኒ ነዋሪዎች ምሽት ላይ በአግባቡ ዘና እንዳንል እንቅፋት ሆኖብናል ያሉት ሕግ ከጥር ጀምሮ እንደሚሻር ተገለጸ።

አወዛጋቢ በነበረው ሕግ፤ ታዋቂ በሆኑ አካባቢዎች በሚገኙ መጠጥ ቤቶች ላይ ሰዓት እላፊ ተጥሎ ነበር። መጠጥ መሸጥ የሚቻልበት ጊዜም በሕግ ተገድቦ ነበር።

ሕጉ ተግባራዊ የተደረገው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2014 ነበር። ሕጉ በመጠጥ ግፊት የሚፈጠሩ ጸቦችን ቢያስቆምም፤ የከተማዋን ድባብ እንዳቀዘቀዘው ተቺዎች ተናግረዋል።

የኒው ሳውዝ ዌልስ መሪ ግላዲየስ በርጂክሊን እንደተናገሩት፤ ሲድኒ ሞቅ ደመቅ እንድትል ይሻሉ። "ከአውስትራሊያ ከተሞች ዓለም አቀፋዊቷ ከተማ መሆናችንን ማንጸባረቅና ጠንካራ የምሽት ገቢ መኖሩን ማረጋገጥ እንሻለን" ብለዋል።

'ኪንግ ክሮስ' በተባለ መዝናኛ አካባቢ ሁለት የ18 ዓመት ወጣቶች መሞታቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰ የሕዝብ ቁጣ ምክንያት ነበር መጠጥ ቤቶች ላይ ሰዓት እላፊ የተጣለው። የወጣቶቹ ሕይወት ያለፈው በመጠጥ በተገፋፋ ግጭት ሳቢያ ነበር።

ክስተቱን ተከትሎ በወጣው ሕግ መሰረት ከ7፡30 በኋላ የምሽት ክለብ መግባትና ከ5፡00 በኋላ መጠጥ መግዛት ታግዶ ነበር።

እገዳው ከተጣለ በኋላ በመጠጥ ግፊት የሚነሱ ግጭቶች ቁጥር ማሽቆልቆሉን ፖሊስና የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ሆኖም ግን ሕጉ የምሽት ገበያ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል ተብሏል። ሕጉ ለ180 የንግድ ተቋሞች መዘጋት ምክንያት መሆኑም ተነግሯል። ለፓርላማ የቀረበ ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ሕጉ የሲድኒን የምሽት ንግድ በማቀዛቀዙ፤ ከተማዋ በዓመት 16 ሚሊዮን ዶላር አጥታለች።