ጉግል ምርቶቹ ላይ ስህተት ላገኘ ሰው 1.5 ሚሊዮን ዶላር ሊከፍል ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
ጉግል በአንድሮይድ ስልኮቹ ላይ ስህተት ለሚያገኝ ሰው የሚከፍለውን ገንዘብ ከ200,000 ዶላር ወደ 1.5 ሚሊዮን ዶላር አሳደገ።
ጉግል በአንድሮይድ ምርቶቹ ላይ በተገጠመው ካሜራ ላይ ከደህንነት ጥበቃ ጋር የተያያዘ ክፍተት ላገኘ ሰው ገንዘቡን እንደሚያበረክት አስታውቋል። ድርጅቱ እንደ ጎርጎሮሳውኑ አቆጣጠር ከ2015 ወዲህ ለደህንነት ጥበቃ ተመራማሪዎች አራት ሚሊየን ዶላር መክፈሉንም ይፋ አድርጓል።
አፕል፣ በዝፊድ፣ ፌስቡክና ሳምሰንግም በምርቶቻቸው ላይ ከደህንት ጥበቃ ጋር የተያያዘ ክፍተት ለሚጠቁም ሰው ገንዘብ ይሰጣሉ። ክፍተቶች ከተጠቆሙ በኋላ ምርቶቹን እንደሚያስተካክሉም ድርጅቶቹ ይናገራሉ።
'ቲታም ኤም' የተባለው መሣሪያ ስልክ የሚከፈትበት መረጃ የሚከማችበትና የስልኩን ደህንነት የሚጠብቅም ነው። አንድ ተመራማሪ የዚህን መሣሪያ ክፍተት ማሳየት ከቻለ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ያገኛል ማለት ነው።
አንዳንድ ተመራማሪዎች፤ የስልክ ምርቶች ላይ ያሉ ክፍተቶችን ማጋለጥ፤ መረጃው በወንጀለኞች እጅ እንዲገባ መንገድ ይከፍታል የሚል ስጋት አላቸው።
ኬቲ ሞሶዎሪስ የተባሉ ተመራማሪ እንደሚሉት፤ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ስህትተ ለሚያጋልጥ ሰው የሚሰጡት ገንዘብ፤ ወንጀለኞች ጥቁር ገበያ ላይ ከሚያቀርቡት ገንዘብ ጋር አይወዳደርም።
ቢቢሲም የደህንነት ክፍተት ለሚጠቁሙ ተመራማሪዎች ገንዘብ ባይሰጥም ልዩ ሽልማት ያበረክታል።












