ስፔን የዜጎቿን እንቅስቃሴ በስልክ መከታተሏ ጥያቄ አስነሳ

ስልክ የምትጠቀም ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በያዝነው ሳምንት፤ የስፔን መንግሥት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስፔናውያንን እንቅስቃሴ በስልካቸው አማካይነት እየተከታተለ ነው።

መንግሥት ሕዝቡን መሰለል ሊጀምር ነው በሚል ብዙዎች ቢተቹም፤ የአገሪቱ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ክትትሉ ለስምንት ቀን ብቻ የሚቆይ ነው ብሏል። ኤጀንሲው እንደገለጸው፤ ክትትሉ ስፔናውያን ቀናቸውን እንዲሁም ምሽታቸውን እንዴት እንደሚያሳልፉ ለማወቅ ያለመ ነው።

በክትትሉ ሦስት የአገሪቱ የቴሌኮም ተቋሞች ተሳታፊ ናቸው። የተጠቃሚዎቻቸውን መረጃ አሳልፈው መስጠታቸው ሕገ ወጥ አለመሆኑንም ገልጸዋል።

በስልክ ክትትል ማድረግ ምን ማለት ነው?

የስታትስቲክስ ኤጀንሲ በመጀመሪያዎቹ አራት ቀናት፤ ዜጎች ወደ ሥራ ወይም ትምህርት ቤት ሲሄዱ እንደሚከታተል፤ ከዛም በእረፍት ቀናትና በበዓል ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ቀጣዩ ክትትል በገና ቀን እና ከክረምት በኋላ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል።

ሦስቱ የቴሌለኮም ድርጅቶች ሞቪስታር፣ ቮዳፎን እና ኦሬንጅ ከስፔን ስልክ ተጠቃሚዎች 78.7 በመቶውን ይሸፍናሉ። በክትትሉ በመሳተፋቸውም 500,000 ዩሮ ይከፈላቸዋል።

5,000 ነዋሪ በሚይዙ 3,200 ክፍሎች፤ ከእኩለ ሌሊት እስከ ንጋት ከዛም ከረፋድ እስከ ምሽት በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ክትትል ይደረጋል።

ዜጎች መቼና የት እንደሚንቀሳቀሱ የሚያሳየው መረጃ ተጠናቅሮ፤ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሻሻል እንደሚውል ኤጀንሲው አሳውቋል። መረጃው ከሦስት ዓመት በኋላ ለሚካሄደው የሕዝብ ቆጠራ ግብዓት እንደሚሆንም ተገልጿል።

የቴሌኮም ድርጅቶቹ እንደሚሉት ከሆነ፤ የሰዎች ግላዊ መረጃ ይፋ ስለማይደረግ የተጠቃሚዎቹን ማንነት ማወቅ አይቻልም።

ተቺዎች ምን ይላሉ?

በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች፤ ክትትሉ የሰዎችን ግላዊ መብት መጋፋት ነው እያሉ ነው። ዴቪድ ማዜቱ የተባሉ የቴክኖሎጂ ጠበቃ፤ የቴሌኮም ድርጅቶች የሰዎችን ግላዊ መረጃ ለስታትስቲክስ ማዋል የለባቸውም ብለዋል።

አንዳንድ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ከክትትሉ ለማምለጥ ስልካቸውን ማጥፋት ወይም 'በረራ ላይ ነኝ' የሚል ቁልፍ በመጫን ከአገልግሎት ውጪ መሆንን አማራጭ አድርገዋል።

የኦሬንጅና ቮዳፎን ተጠቃሚዎች መረጃቸው ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ ኢሜል እየላኩም ነው።

በሌላ በኩል የጉግልን ካርታ፣ ፌስቡክ እና አማዞንን በየቀኑ የሚገለገሉ ሰዎች እስካሁን ቅሬታ ሳያሰሙ፤ አሁን የመንግሥት ክትትል ላይ ጥያቄ ማንሳታቸው ያልተዋጠላቸውም አሉ።

የመረጃ ደህንነት ባለሙያ ጆሴ ሮሴል እንደሚሉት፤ ስልኮች ከ10 እስከ 20 የሚደርሱ እንቅስቃሴን የሚከታተሉ መሣሪያዎች አሏቸው። ተጠቃሚዎች ያሉበትን ቦታ የሚጠቁም መሣሪያ፣ ካሜራ እንዲሁም ማይክራፎንም ባለው ስልክ እንደሚገለገሉም ያስረዳሉ።

በርካታ አገሮች የስልክ ግንኙነቶች ለስለላ እና የቴሌኮም ግንኙነትን ለማቋረጥ ጥቅም ላይ ይውላሉ የሚል ስጋት አላቸው። አሜሪካን ጨምሮ ሌሎችም አገሮች ቻይና ሠራሹን ሁዋዌ ለማገድ ካቀረቧቸው ምክንያቶች አንዱ ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም የሚለው መከራከሪያ ነጥብ ነው።