የቻይናን መንግሥት የወቀሱት አውስትራሊያዊያን ፖለቲከኞች ወደ ቻይና ድርሽ እንዳይሉ ተከለከሉ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES/LIBERAL PARTY
ሁለት አውስትራሊያውያን ፖሊተከኞች ወደ ቻይና እንዳይገቡ ተከልክለዋል።
አንድሪው ሃስቲ እና ጄምስ ፓተርሰን የተባሉት እኒህ የአውስትራሊያ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ለትምህርታዊ ጉበኝት ወደ ቻይና ሊሄዱ በመሰናዳት ላይ ነበሩ።
ቻይና ለመሄድ የቪዛ ማመልከቻ ያስገቡት አውስትራሊያውያን በቻይና ኤምባሲ ተከልክለዋል። የኤምባሲው ምክንያት ደግሞ ፖለቲከኞቹ የቻይና መንግሥትን ወቅሰዋል የሚል ነው። ኤምባሲው፤ ፖሊተከኞቹ አስተያየታቸውን በይፋ እስካልሻሩ ድረስ የቻይና ቪዛ አንሰጥም ብሏል።
ሁለቱም ፖለቲከኞች ቻይና መሄድ በአፍንጫችን ይውጣ እንጂ አስተያየትችን አንሽርም ሲሉ ተደምጠዋል።
የአውስትራሊያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ አባል የሆኑት ሁለቱ ፖለቲከኞች የቻይና መንግሥትን በተለይ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ሲወቅሱ ብዙ ጊዜ ይሰማሉ። አልፎም የቻይና መንግሥት በአውስትራሊያ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ እየገባ ነው ባይ ናቸው።
ሌላ ወደ ቻይና ሊያመራ ያሰበ አንድ ፖለቲከኛ ግን ቪዛ እንዳልተከለከለ መረጃዎች እየወጡ ነው።
ቻይና በአውስትራሊያ ፖለቲካ እጇን እያስገባች ነው የሚለው ጉዳይ ቀንደኛ መነጋገሪያ ሆኗል። ምንም እንኳ ይህ ወቀሳ ውሃ አያነሳም፤ እንደውም ቻይናውያን ላይ ጥላቻ ሊዘራ ይችላል የሚሉ ባይጠፉም።
ጉዳዩ መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ መግለጫ ያወጡት የቻይና ኤምባሲ ቃል-አቀባይ ሃገራቸው ቻያና ጠል አስተያየት ለሚሰጡ ሰዎች ቪዛ እንደማትሰጥ አስረግጠዋል።
አንድሪው ሃስቲ የተሰኙት ፖለቲከኛ ባለፈው ነሃሴ ሲድኒ ሞርኒንግ በተባለው ጋዜጣ ላይ ያወጡት ፅሑፍ የቻይና መንግሥት አምባገነን ሆኗል፤ አውስትራሊያም ይህን ማየት ተስኗታል ሲሉ በመውቀሳቸው ነው ቪዛ የተከለከሉት። ሌላኛው ፖለቲከኛም በተጋጋሚ መሰል ሃሳብ ሲሰጡ ተስተውለዋል።
ጎረቤታሞቹ ቻይና እና አውስትራሊያ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዓይንና ናጫ ሆነዋል።













