የትዊተር የቀድሞ ሠራተኞች ለሳዑዲ በመሰለል ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሁለት የቀድሞ የትዊተር ሠራተኞች ለሳዑዲ አረቢያ በመሰለል ተጠርጥረው አሜሪካ ውስጥ ተከሰሱ።
ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ ይፋ በተረገው ክስ፤ የሳዑዲ ወኪሎች፤ ሳዑዲን በመተቸት የሚታወቁ ግለሰቦችን ጨምሮ ስለ ትዊተር ተጠቃሚዎች የግል መረጃ መጠየቃቸው ተመልክቷል።
ተከሳሾቹ አህመድ አቡአማኖ የተባለ አሜሪካዊ እና አሊ አልዛባራህ የተባለ የሳዑዲ ዜጋ ሲሆኑ፤ አህመድ አልሙታይሪ የተባለ የሳዑዲ ዜጋም በስለላ ተጠርጥሯል።
አህመድ አልሙታይሪ በሁለቱ የቀድሞ የትዊተር ሠራተኞችና በሳዑዲ ባለሥልጣኖች መካከል ተላላኪ እንደነበረ በክሱ ተገልጿል።
አህመድ አቡአማኖ ባለፈው እሮብ ሲያትል በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን፤ የፊታችን አርብ በድጋሚ እስኪቀርብ ድረስ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ይቆያል። ለአሜሪካው የምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ ሀሰተኛ ሰነድ እና መረጃ በመስጠትም የተከሰሰው አህመድ፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2015 ላይ ከትዊተር መልቀቁ ተገልጿል።
አሊ አልዛባራህ እና አህመድ አልሙታይሪ ሳዑዲ ውስጥ እንደሚገኙ ይታመናል።
የቀድሞ የትዊተር ኢንጂነር አሊ አልዛባራህ በሳዑዲ ልዑካን ከተመለመለ በኋላ፤ በ2015 ከ 6,000 በላይ የትዊተር ተጠቃሚዎችን መረጃ ማግኘቱ ተገልጿል።
በዚህ ምክንያት ኃላፊዎቹ ከሥራ ሲያስወጡት፤ ባለቤቱና ልጁን ይዞ ወደ ሳዑዲ ኮብልሏል።
ትዊተር "አገልግሎቴን ለማደናቀፍ ምን ያህል ርቀት አንደሚኬድ አይቻለሁ" ሲል በጉዳዩ ዙርያ መግለጫ ሰጥቷል። ባለሥልጣኖችን ተጠያቂ ለማድረግ እና ሀሳባቸውን ለመግለጽ ትዊተርን የሚጠቀሙ ግለሰቦችን ደህንነት የሚጠብቅ አሠራር እንዳለውም አክሏል።
ሳዑዲ በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ አጋር አገር መሆኗ ይታወቃል።
የጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂን ግድያ ተከትሎ መላው ዓለም ሳዑዲን ቢያወግዝም፤ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሳዑዲ ጋር የቅርብ ወዳጅ ናቸው።












