አምነስቲ፡ አሜሪካ በአየር ጥቃቷ በስህተት የሶማሌ አርሶ አደሮችን ገድላለች

በሶማሊያ የተገደሉት አርሶ አደሮች መኪና

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

መጋቢት ወር ላይ አሜሪካ ባደረገችው የአየር ጥቃት የተገደሉት አርሶ አደሮች መሆናቸውን አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ አስታውቋል።

በወቅቱ የአሜሪካ ጦር አፍሪካ እዝ (አፍሪኮም) ታጣቂዎችን ገደልኩ ቢልም በተደረገው ማጣራት በወቅቱ መኪናው ውስጥ ሲጓዙ የነበሩት ንፁኃን ዜጎች ናቸው ተብሏል።

የተገደሉት ሶስቱ ግለሰቦች አርሶ አደሮችና ከአልሻባብም ጋር ይሁን ከየትኛውም ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት የነበራቸው አለመኖሩን አሜሪካ ለማጣራት ተስኗታል በማለት አምነስቲ ይተቻል።

ሶስቱ አርሶ አደሮች የግብርና ተግባራቸውን አከናነው ወደቤታቸው ሲመለሱ መኪናቸው ላይ ጥቃት እንደደረሰባቸው አምነስቲ አስታውቋል።

የሟቾቹ የስራ ባልደረቦችና ቤተሰቦችን ጨምሮ አስራ አንድ ሰዎች ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሲሆን ሁሉም ቢሆን ግለሰቦቹ ከአልሻባብ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል።

"የአሜሪካ ጦር የአፍሪካ ዕዝ በጥቃቱ ማንን ኢላማ እንደሚያደርግ ሳያውቅ በደመ ነፍስ እየተራመደ ነው፤ ግለሰቦችንም በመግደል እንዲሁም ሚስጥራዊ ጦርነት በሶማሊያ ላይ በማካሄድ ናቸው" በማለት በሶማሊያ የአምነስቲ ተመራማሪ የሆነው አብዱላሂ ሃሰን በመግለጫቸው ገልፀዋል።

አፍሪኮም በበኩሉ ባደረጉት ግምገማ የአየር ጥቃቱ የገደለው "ሶስት አሸባሪዎች" መሆኑን አስታውቆ የንፁኃን ዜጎች ተገድለው ሊሆን ይችላል የሚለው ሪፖርት ደርሶኛል ብሏል።

የአፍሪኮም ቃል አቀባይ ጆን ማንሌይ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት " የአሜሪካ ጦር የአፍሪካ እዝ ተሽከርካሪውም ሆነ በውስጡ የነበሩ ተሳፋሪዎች የአልሻባብ አባላትና እንዲሁም የአልሻባብን እንቅስቃሴ የሚደግፉ መሆናቸውን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እርግጠኞች ነበርን" ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም የአሜሪካ ጦር የአፍሪካ እዝ ንፁኃን ዜጎች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቀነስ ዘዴዎችን ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

አሜሪካ በሶማሊያ የምታደርገው የአየር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደቡባዊት ሶማሊያ ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር አለብን ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

በዚህ በያዝነው አመትም የአየር ጥቃቶች መጨመራቸው ተገልጿል።

በትናንትናው ዕለት የአልሸባብ ታጣቂዎች የአሜሪካን የጦር ሰፈር ያጠቁ ሲሆን በዚህም ቦታ አሜሪካ ሶማሊያውያን የጦር ኮማንዶዎችን የምታሰለጥንበት መሆኑ ተገልጿል።