የሱዳን ተቃዋሚዎችና የሽግግር መንግሥቱ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ላይ ተስማሙ

የሱዳን ተቃዋሚዎችና ወታደሩ በመስማማታቸው ወጣቶች ደስታቸውን በአደባባይ ሲገልፁ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

ሱዳንን እያስተዳደረ የሚገኘው ወታደራዊ መንግሥትና የተቃዋሚዎች ጥምረት የሽግግር መንግሥት ለመመስረት መንገድ ይጠርጋል የተባለለት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ላይ መስማማታቸው ተሰማ።

ከአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪ ሆነው የቀረቡት ሞሐመድ ሐሰን ሌባት ስምምነት ላይ መደረሱን ይፋ ያደረጉ ሲሆን ዝርዝር ጉደዮች ላይ ግን ያሉት ነገር የለም።

"ለሱዳን ሕዝብ፣ ለአፍሪካውያንና ለዓለም አቀፍ አካላት የማበስረው ሁለቱ ተወካዮች በሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ላይ ሙሉ በሙሉ መስማማታቸውን ነው።"

አክለውም ሁለቱ አካላት ስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ከማኖራቸው በፊት አንዳንድ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ለመስራት ቀጣይ ስብሰባዎች እንደሚኖሩ ተናግረዋል።

ሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር በሚያዚያ ወር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሰላም ርቋት ትገኛለች።

በሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌው ላይ እየተካሄደ የነበረው ንግግር በመራዘሙ በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል።

ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ይህ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ስምምነት ላይ መደረሱ እንደተሰማ የሱዳን ጎዳናዎች ደስታቸውን በሚገልጡ ሰዎች ተሞልተዋል።

በሱዳን ለመጀመሪያ ጌዜ ተቃውሞ መሰማት የጀመረው በታህሳስ ወር ሲሆን ለተቃውሞውም ሰበብ የነበረው በወቅቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኦማር አልበሺር ጥለውት የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ ነው።

ከዚያም በኋላ ለረዥም ጊዜ በመከላከያ ዋና መስሪያ ቤት ደጃፍ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ ቆይተው በሚያዚያ ወር ፕሬዝደንት አል በሺር ከሥልጣን ተወግደዋል።

ከእርሳቸው ከሥልጣን መነሳት በኋላ ደግሞ ሥልጣን ለሲቪሉ ይሰጥ በሚል ተቃውሞዎች ሲደረጉ ነበር።

የስምምነቱን ረቂቅ የተመለከተው ሮይተርስ የዜና ወኪል በርካታ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን በመግደል የሚከሰሰው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጦር ኃይሉ ትዕዛዝ ሥር ይሆናል መባሉን ዘግቧል። የደህንነት ተቋሙም በሉዓላዊ ምክር ቤቱና በካቢኔው ቁጥጥር ይደረግበታል የሚለው የስምምነቱ አካል መሆኑን አክሎ ዘግቧል።

ይህ ስምምነት የተደረሰው ዘጠኝ የፈጥኖ ደራሽ አባላቱ ተማሪዎችን በመግደል ከሥራቸው መሰናበታቸውንና በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ከተገለፀ በኋላ ነው።

ከዚህ በፊት ወታደሩና ተቃዋሚዎች በርካታ ስምምነቶች ላይ ደርሰዋል።