ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ወደ ሱዳን ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሱዳን ካርቱም ሊያቀኑ መሆኑን ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ያደረገው ሱዳን ትሪቡን ገለፀ።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የአሁኑ ጉዟቸው ዓላማ በሱዳን ወታደራዊ የሽግግር መንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲው ኤፍ ኤፍ ሲ መካከል እየተካሄደ ያለውን የድርድር ሁኔታ ለመከታተል ነው።
ከሁለት ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ሱዳን አቅንተው የነበረ ሲሆን ተቃዋሚ ፓርቲውንና ወታደራዊ የሽግግር መንግሥቱን በተናጠል ማነጋጋራቸው ይታወሳል። በመሆኑም ጠቅላይ ሚንስትሩ አሁንም ሁለቱ አካላት ረቂቅ ስምምነቱ ላይ እንዲግባቡ ያነጋግሯቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ወገኖች ሉዓላዊ የሆነ ምክር ቤት ለማቋቋም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በሱዳን የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መልዕክተኛ ማህሙድ ድሪር ተናግረዋል። ይህ ምክር ቤት ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት አገሪቷን የሚያስተዳድር ነው።
አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል በበኩላቸው ምክር ቤቱ ስምንት ሲቪልና ሰባት ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲኖሩትና በመፈራረቅ የፕሬዚደንትንት ሚና እንዲጫወቱ ኢትዮጵያ ሃሳብ አቅርባለች ብለዋል።
የወታደራዊ ሽግግር መንግሥቱ ዋና ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን አገሪቱን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር ከተቃዋሚ ፓርቲው ጋር ለመደራደር ዝግጁ እንደሆኑ ባለፈው ረቡዕ ገልፀው ነበር።
ይሁን እንጂ የፀጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎችን በኃይል ለመበተን በወሰዱት ርምጃ ምክንያት የሁለቱ ወገኖች ድርድር ሳይሳካ ቀርቷል።
በመንግሥት ሥር የሚተዳደረ ሱና የተባለው የዜና ወኪል ሌተናን ጀኔራል ቡርሃንን ጠቅሶ እንደዘገበው የሽግግር መንግሥቱ ድርድሩን ለማጠናቀቅ ዝግጁ እንደነበር አስታውቋል።














