ትራምፕ ኪም ጆንግ ኡንን አግኝተው "ሰላም" ለማለት እንደሚፈልጉ ገለፁ

ከጦር ሰራዊት እንቅስቃሴ ነፃ የሆነውን ቀጠና ወታደሮች ሲጠብቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሰሜን ኮሪያውን መሪ ሰሜንና ደቡብ ኮሪያን በሚለየው ድንበር ላይ ለማግኘት እንደሚፈልጉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አሳወቁ።

የፕሬዝዳንቱ ያልተጠበቀ የትዊተር መልዕክት ኪምን ደቡብ ኮሪያን በሚጎበኙበት ወቅት ወደ ድንበሩ ጎራ በማለት "ሰላም ለማለት" እንደሚፈልጉ የሚገልፅ ነው።

ሰሜን ኮሪያም በምላሹ "አስደሳች" ስትል ገልፃዋለች።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጃፓን ከተካሄደው የቡድን 20 ሃገራት ስብሰባ በኋላ በቀጥታ ወደ ደቡብ ኮሪያ የሄዱት የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ ለመወያየት ነው።

ከዚያም ባልተጠበቀ ሁኔታ ከፕሬዝዳንት ኪም ጋር ለመነጋገር እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጃፓን ኦሳካ የቡድን 20 ሃገራት ስብሰባ ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ እየሰጡ በነበረበት ወቅት ከኪም ጋር "ለመገናኘት እንደሚያስቡ" ተናግረዋል።

"ለሁለት ደቂቃ ከተገናኘን በቂ ነው" በማለት ለሪፖርተሮች ተናግረዋል። ከዚህ አስተያየት በፊት ከሳዑዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ጋር ቁርስ እየበሉ ስለሥራ እንሚያወሩ ገልፀው ነበር።

እስካሁን ያልታወቀው ጉዳይ የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ከሰሜን ኮሪያ ጋር መነጋገር እንደሚፈልጉ ቀድሞ ይነገራቸው ወይም አይነገራቸው ነው።

ሰሜን ኮሪያ ይህ የትራምፕ ሃሳብ በትዊተር ገፃቸው ላይ እንደሰፈረ በምክትል ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስተያየቷን ሰጥታለች።

"ምንም እንኳ በዚህ ጉዳይ ላይ ይፋዊ ግብዣ ባይቀርብልንም እንደ ጥሩ አማራጭ እንቀበለዋለን" በማለት እንዲህ ዓይነት ስብሰባ "የሁለቱን ሃገራት መሪዎችንና የሃገራቱንም የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሚያጠናክር " ተናግረዋል።

የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ገና ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም ያሉ ሲሆን በሰሜን ኮሪያና በአሜሪካ መካከል ያለው ውይይት እንደማይለወጥ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።

ትራምፕ ሁለቱ ኮሪያዎችን የሚለየውንና ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ የሆነውን ቀጠና ለመጎብኘት በ2017 ህዳር ወር ላይ አቅደው የነበረ ቢሆንም በአየር ጠባዩ አለመመቸት የተነሳ ዕቅዳቸው ተሰርዞ ነበር።