ሰሜን ኮሪያ ለአሜሪካ የኮቪድ ክትባት ልገሳ ጥያቄ ምላሽ እንዳልሰጠች ፕሬዚዳንት ባይደን ገለጹ

ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ መከሰቱን ይፋ ያደረገችው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመታገል የኮቪድ ክትባቶችን ለመለገስ አሜሪካ ጥያቄ ብታቀርብም ምላሽ አለመስጠቷን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስታወቁ።

በሰሜን ኮሪያ ወደ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በ "ትኩሳት" ህመም መያዛቸውን እና በአገር አቀፍ ደረጃ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን የሃገሪቱ የመንግስት ሚዲያ ዘግቧል።

በአገሪቱ የኮቪድ-19 አነስተኛ ምርመራ እንዲሁም የክትባት አቅርቦት ባለመኖሩ ሁኔታዎችን ፈታኝ አድርጎታል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለሰሜን ኮሪያ ክትባት የማቅረብ ጥያቄን በተመለከተ የተናገሩት በደቡብ ኮሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

"ለሰሜን ኮሪያ ብቻ ሳይሆን ለቻይናም ክትባቶችን አቅርበናል። ይህንንም ወዲያውኑ ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጅተናል" በማለት ፕሬዚዳንት ባይደን ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ጋር በጋራ በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

"ምንም ምላሽ አላገኘንም።" ብለዋል አክለው ፕሬዚዳንቱ

ከአለም ተነጥሎ የሚገኘው የሰሜን ኮሪያ አስተዳደር ከዚህ ቀደም የአለም አቀፍ የክትባት መጋራት መርሃ ግብር አካል የሆነውን ኮቫክስ እንዲሁም የደቡብ ኮሪያና የሌሎች አገራት የክትባቶችን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ተዘግቧል።

ይልቁንስ ድንበሮችን በመዝጋት በተሳካ ሁኔታ የኮሮናቫይረስ እንዳይገባ መከላከል እንደቻለች ያስታወቀች ሲሆን ባለሙያዎች በበኩላቸው ቫይረሱ ለተወሰነ ጊዜ በአገሪቱ መቆየቱን ያምናሉ።

ከሰሞኑ የመንግሥት ሚዲያዎች በዕፅዋት የተቀመመ ሻይ፣ ጨውና ውሃ በመቀላቀል መጉመጥመጥ እና እንደ አይቦፕሮፊን ያሉ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን እንዲወስዱ ምክር እየለገሱ ይገኛሉ።

የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባለሥልጣናቱ የብሔራዊ መድሐኒት ክምችቶችን እያከፋፈሉ ነው ሲሉ ከሰዋል።

ቻይናም በተመሳሳይ መልኩ በከፍተኛ ፍጥረት በሚተላለፈው የአሚክሮን ልውጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ማዕበል ለመቆጣጠር እየታገለች ትገኛለች።

በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም ከእንቅስቃሴ ተገድበው ይገኛሉ።

በደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሴኡል በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፕሬዝዳንት ባይደን የሰሜን ኮሪያው መሪ ጋር ለመገናኘት ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ለዚህም ፕሬዚዳንቱ ያስቀመጡት መስፈርት መሪው "በቅንነት ላይ የተመሰረተ" ከሆነ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።