ዜሌንስኪ ጦርነቱን ማቆም የሚቻለው "በዲፕሎማሲ ብቻ ነው" አሉ

ታትሟል

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በሃገራቸው ያለው ጦርነት ሊቆም የሚችለው "በዲፕሎማሲ ብቻ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያቸው ቀርበው ንግግር ያደረጉት ፕሬዝደንቱ በጦርነት አውድማ ሩሲያን መርታት እንደማይሳናቸው ተነግረዋል።

ነገር ግን አሉ ፕሬዝደንቱ፤ ጦርነቱ ፍፃሜ ሊያገኝ የሚችለው "ቁጭ ብለን ስንደራደር ነው።"

ይህ በእንዲህ እንዳለ ስቬሮድኔስክ በተባለችው የዩክሬን አውራጃ የሚደረገው ጦርነት እንደቀጠለ ነው።

የሩሲያ ኃይሎች ይህችን ቀጠና ሙሉ በሙሉ ለመያዝ ወታደራዊ እርምጃቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

የአውራጃዋ ገዥ ስሪሂ ሃይዲ እንደሚሉት ሩሲያዊያን ሥፍራውን ከጥቅም ውጭ አድርገው ለመያዝ ነው ያቀዱት።

በምስራቃዊቷ የወደብ ከተማ ማሪዮፖል የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት መጠናቀቁ ሩሲያዊያን ወታደሮች ወደ ሌሎች አካባቢዎች አጋዥ ጦር ሆነው እንዲዘምቱ አስችሏቸዋል።

የቢቢሲው ወኪል ጄምስ ዋተርሃውስ እንደሚለው ሩሲያ በምድርና በሰማይ እንዲሁም በሚሳዔል በመታገዝ የምታደርሰውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።

ወኪሉ አክሎ ሉሃንስክ አካባቢ የሩሲያ ወታደሮች ይዞታቸውን ሲያሰፉ የዩክሬን ጦር ደግሞ እያፈገፈገ ነው።

የዩክሬኑ መሪ ዜሌንስኪ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር "ጦርነቱ እስካለ ድረስ ደም አፋሳሽ መሆኑ ይቀጥላል ነገር ግን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሊቋጭ ይችላል" ብለዋል።

ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች አሳልፈው መስጠት የማይሿቸው ጉዳዮች ስላሉ ዲፕሎማሲው ቀላል እንደማይሆን ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል።

ባለፈው ማክሰኞ የዩክሬኑ ተደራዳሪ ሚካይሎ ፖዶሊያክ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ድርድር ለጊዜው እንደቆመ ተናግረው ነበር።

ረቡዕ ዕለት ደግሞ የክሬምሊን ቃል አቀባይ የሆኑት ድሚትሪ ፔስኮቭ የኪዬቭ ባለሥልጣናት ድርድሩን አይሹትም ሲሉ ወቅሰው ነበር።

የሩሲያ ዜና ወኪሎች ለመጨረሻ ጊዜ ድርድር የተካሄደው ከአንድ ወር በፊት ነው ሲሉ አስነብበዋል።

መቋጫ ባልተገኘለት በዚህ ጦርነት አሜሪካ ወታደራዊ፣ ኢኮሚያዊና ሰብዓዊ እርዳታዋን ማድረስ ቀጥላለች።

ቅዳሜ ዕለት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን 40 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት እርዳታ ለዩክሬን እንዲደረግ የሚያዝ ደብዳቤ በፊርማቸው ማፅደቃቸውን ዋይት ሃውስ አስታውቋል።

ይህ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የተደረገ ትልቁ እርዳታ ይሆናል ማለት ነው።

ከዚህ ድጋፍ 6 ቢሊዮን ዶላር ያክሉ ለብረት ለብስ መኪና አየር መቋቋሚያ የሚሆን ነው።

ቅዳሜ ዕለት የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ወደ ሩሲያ እንዳይገቡ ከተከለከሉ 900 አሜሪካዊያን መካከል ይገኛሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከንና የሲአይኤ መሪ ዊሊያም በርንስ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።