ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ያሉበትን ማወቅ እንዳልቻሉ ባለቤታቸው ተናገሩ

ታትሟል

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ አዲስ አበባ ውስጥ ከቤታቸው እንደወጡ አለመመለሳቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ መነን ኃይሌ ለቢቢሲ ገለፁ።

ወ/ሮ መነን ስለ ባለቤታቸው ሲናገሩ ትናንት ሰኞ ግንቦት 08/2014 ዓ.ም. ከቤታቸው 5፡15 አካባቢ የወጡት ከጓደኛቸው ጋር ቀጠሮ እንደነበራቸው ገልፀው መሆኑን ያስረዳሉ።

ከዚያ በኋላ ግን ወደ ቤታቸው ባለመመለሳቸው ደጋግመው ወደ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ቢደውሉም ምላሽ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።

ጄኔራል ተፈራ ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ያገለገሉ ሲሆን እንዲሁም በቅርቡ የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ሆነው መስራታቸው ይታወሳል ።

እንደ ወ/ሮ መነን ገለፃ ከሆነ ጄኔራል ተፈራ ያገኟቸው ሰዎች በዕለቱ አስከ 10 ሰዓት ድረስ አብረው መቆየታቸውን እና ከዚያ በኋላ እንደተለያዩ ነግረዋቸዋል።

ከዚያ በኋላ ግን የደረሱበትን ለማወቅ እንዳልቻሉ ባለቤታቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ጄኔራል ተፈራ ሞሞ ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥነት ከተነሱ በኋላ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ አስተያየታቸውን ይሰጡ ነበር።

ወ/ሮ መነን የባለቤታቸውን መጥፋት አስመልክቶ ወደ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲሁም አዲስ አበባ ፖሊስ በመሄድ ቢጠይቁም ግለሰቡ "በቁጥጥራቸው ስር እንደማይገኝ" እንደገለፁላቸው ይናገራሉ።

በአሁኑ ሰዓትም ባለቤታቸውን ለማግኘት ሊኖሩበት ይችላሉ ወደተባሉ የተለያዩ የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማት በመሄድ ፍለጋቸውን መቀጠላቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

ጄኔራል ተፈራ ማሞ ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት ናቸው።

ጄኔራል ተፈራ የስኳር ሕመምተኛ መሆናቸውን የገለፁት ባለቤታቸው የታዘዘላቸውን መድኃኒት እየወሰዱ አንደነበር አመልክተው፣ መድኃኒታቸውን ካልወሰዱ አንደሚታመሙ በመጥቀስ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሚኖሩበት ባሕርዳር ወደ አዲስ አበባ የመጡት በእግራቸው ውስጥ የሚገኙትን ጥይቶች በተመለከተ የሕክምና ክትትል ለማድረግ እንደነበረም ጨምረው አስረድተዋል።

"እስሩን ለምዶታል ያለፈበትም ነው፤ የሚያሳስበን የጤናው ሁኔታ ነው" ብለዋል።

የሌ/ጄኔራል ተፈራ መሰወርን በተመለከተ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምንም መረጃ እንደሌለው ለቢቢሲ ተናግሯል።

የመዲናዋ ፖሊስ የሕዝብ ግነኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፤ "በዚህ ላይ መረጃው የለኝም። ከጠፉ 24 ሰዓት ከሞላቸው የቤተሰብ አባላት መጥፋታቸውን ማስዘመዝገብ ይችላሉ። እኛም በአስሩም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች እናሳውቃለን። ከታስረው የሚገኙ ከሆነ ያሉበትን እናሳውቃለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ለዓመታት በከፍተኛ መኮንንነት ያገለገሉት ብርጋዲዬር ጄነራል ተፈራ ማሞ ከአስር ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ አሲረዋል በሚል ከሌሎች ጋር ተከሰው ለዓመታት በእስር ላይ ቆይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎም ከእስር ተለቀው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በቅርቡም የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመግባት ጥቃት በሰነዘሩበት ጊዜ የክልሉን ልዩ ኃይል በበላይነት ሲመሩ የነበሩ ሲሆን፣ ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ ከዚሁ ኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጋቸው ይታወሳል።