ማክዶናልድስ ከ30 ዓመታት አገልግሎት በኋላ ከሩሲያ ነቅሎ ወጣ

ማክዶናልድስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ማክዶናልድስ የተሰኘው ፈጣን ምግብ አቅራቢ ድርጅት ከ30 ዓመታት በኋላ ከሩሲያ ነቅሎ እየወጣ ነው።

አንጋፋው አሜሪካዊ ድርጅት ሩሲያ የተከላቸውን ፈጣን ምግብ መሸጫ ሱቆች እየሸጠ ነው።

ኩባንያው ሩሲያ ዩክሬንን ለምን ወረረች በማለት ባለፈው መጋቢት 850 ሱቆቹን መዝጋቱ የሚዘነጋ አይደለም።

ይህ ግዙፍ በርገርና የድንች ጥብስ (ቺፕስ) በመሸጥ የሚታወቅ ድርጅት በዩክሬን ያለው "ሰብዓዊ ሁኔታ" እንዲሁም ጦርነቱ የሚያመጣው "አስቸጋሪ ክስተት" ከሩሲያ ነቅዬ እንድወጣ አድርገውኛል ሲል ገልጦ ነበር።

ማክዶናልድስ በፈረንጆቹ 1990 ቅርንጫፉን ሞስኮው ሲከፍት በአሜሪካና ሩሲያ መካከል የነበረው ቀዝቃዛው ጦርነት ተገባደደ ተብሎ ነበር።

በቀጣዩ ዓመት ሶቪዬት ሕብረት ፈረሰች፤ ሩሲያም ምጣኔ ሃብቷን ለምዕራባዊያን ኩባንያዎች ከፈተች።

ነገር ግን ከ30 ዓመታት በኋላ ይህ ግዙፍ ኩባንያ 850 ሱቆቹን ዘግቶ ከሩሲያ ጠራርጎ መውጣቱ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል።

የማክዶናልድስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክሪስ ኬምፕዚንስኪ "ይህ በጣም ውስብስብ ውሳኔ ነው፤ ተፅዕኖውም ከፍ ያለ ነው" ሲሉ ለሠራተኞቻቸው መልዕክት ልከዋል።

"አንዳንዶች ምናልባት ምግብ ማቅረባችን፤ ሺዎችን መቅጠራችን ትክክል ነው ብለው ያስባሉ" ሲሉ ክሪስ አክለዋል።

"ነገር ግን. . ." አሉ ክሪስ "ነገር ግን ሰብዓዊ ቀውሱን እንዲሁ በቀላሉ የምንዘጋው አይደለም። ወርቃማው አርማችንም የዚህ መገለጫ አይደለም" ብለዋል።

ማክዶናልድስ የገዛቸውን መሬቶች ለሩሲያዊያን መልሶ እንደሚሸጥ አስታውቋል።

ቢሆንም ከሁሉም ሱቆቹ ስሙንና የምግብ ዝርዝር ማሳያውን [ሜኑ] ይዞ እንደሚሄድ አስታውቋል።

ግዙፉ ትኩስ ምግብ አቅራቢ ድርጅት ሱቆቹ ገዥ እስኪያገኙ ድረስ ሠራተኞቹ ደሞዝ እንዲከፈላቸው እንደሚያደርግ ገልጧል።

ማክዶናልድስ ከሩሲያ ነቅሎ በመውጣቱ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ሊያጣ እንደሚችል ተነግሯል።

ሩሲያ እንደ ማክዶናልድስ ያሉ ኩባንያዎች ነቅለው መውጣታቸው የምዕራባዊያን ሤራ ነው ትላለች።

ሬኖልት የተሰኘው መኪና አምራች ኩባንያም እንዲሁም ከሩሲያ ነቅሎ ሊወጣ እንደሆነ መግለጡ አይዘነጋም።

ይህ የፈረንሳይ ኩባንያ ማምረቻ ኩባንያውን ሸጦ የተወሰነውን ገንዘብ ለሩሲያ ሳይንስ ተቋም የተቀረውን ደግሞ ለሞስኮ ከተማ ለመለገስ ቃል ገብቷል።

ነገር ግን ሩሲያ የሬኖልት ንብረት አሁን የመንግሥት ሆኗል በማለት የድርጅቱን ንብረት ጠቅልላለች።

ባለፈው ዓመት ከማክዶናልድስ ገቢ 9 በመቶ የሚሆነውን የሸፈኑት ሩሲያና ዩክሬን ነበሩ።

ኩባንያው ዩክሬን ውስጥ የገነባው ቅርንጫፍ በጦርነቱ ምክንያት አገልግሎት እየሰጠ ባይሆንም ለሠራተኞቹ ደመወዝ እየከፈለ ነው።

ስታርባክስ፣ ኮካ ኮላ፣ ሊቫይስ እንዲሁም አፕል ሩሲያ ውስጥ ያላቸውን እንቅስቃሴ ካቆሙ አሊያም ካቋረጡ ድርጅቶች መካከል ናቸው።

የተወሰኑ ድርጅቶች ደግሞ በተወሳሰበ ስምምነት ምክንያት ሥራችንን ማቆም አንችልም ብለዋል።