የክርስቲያን መሪዎች በፍልስጤማዊቷ ጋዜጠኛ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዙ

ታትሟል

በእየሩሳሌም የሚገኘው የቫቲካን ተወካይ እስራኤል የእምነት ነፃነትን ለማስከበር የገባችውን የአስርት ዓመታት ስምምነት "በአሳዛኝ ሁኔታ እየጣሰች ነው" ሲሉ ከሰዋል።

ተወካዩ ይህንን ያሉት ጥምር ዜግነት ያላት፣ ፍልስጤም አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ሺሪን አቡ አቅላ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ባለፈው ሳምንት አርብ የእስራኤል ፖሊስ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ነው።

በሴንት ጆሴፍ ሆስፒታል ለሃዘን በተሰበሰበው ህዝብ ላይ የእስራኤል መኮንኖች በዱላ ድብደባዎችን ከመፈጸም በተጨማሪ የጎማ ጥይቶችን ተኩሰዋል እንዲሁም አስለቃሽ የጭስ ጋዞችን ተጠቅመዋል።

በኢየሩሳሌም ተወካይ የሆኑት ሞንሲኞር ቶማስ ግሪሳ ድርጊቱ ፍትሃዊ ያልሆነ እና ምክንያታዊ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል።

የክርስትና እምነት ተከታይ የነበረችው አንጋፋዋ የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ሺሪን በእስራኤል ጦር በቁጥጥር ስር በምትገኘው ዌስት ባንክ ከእስራኤል በኩል በተተኮሰባት ጥይት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት መገደሏ ይታወሳል።

በእየሩሳሌም የሚገኙ 15 የእምነት ተቋማት መሪዎች በሴንት ጆሴፍ ሆስፒታል ሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የእስራኤል ፖሊሶች በጋዜጠኛዋ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ያደረሱትን ጥቃት፣ "ሁከት የተሞላበት ጣልቃገብነት" ሲሉ አውግዘዋል።

የእስራኤል ፖሊስ በቤተክርስቲያኑ መሪዎች መግለጫ ላይ ምላሽ ከመስጠት የተቆጠበ ሲሆን የቀብር ሥነ ሥርዓቱን አያያዝ በተመለከተ ግምገማ እንደሚደረግ አስታውቋል።

ሞንሲኞር ግሪሳ እንዳሉት በአውሮፓውያኑ 1993 በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በእስራኤል መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት "የሰዎችን የእምነት መብት መከበር ቢኖርበትም በዚህ ጥቃት ግን ከፍተኛ ጥሰት ተፈጽሟል" ብለዋል።

በኢየሩሳሌም የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በበኩላቸው "የእስራኤል ፖሊስ ወረራ እና ተመጣጣኝ ያልሆነ የሃይል እርምጃ ወስደዋል። ሃዘንተኞችን በማጥቃት፣ በዱላ በመምታት፣ አስለቃሽ የጭስ ጋዞችን በመጠቀም፣ የጎማ ጥይቶችን በመተኮስና የሆስፒታል ህሙማንን በማስፈራራት መሰረታዊ የሰብአዊ መብት የሆነውን የእምነት ነፃነትን ጨምሮ የዓለም አቀፍ ደንቦችን እና መመሪያዎችን በእጅጉ ጥሰዋል" ብለዋል።