ዘ ኢኮኖሚስት ዘጋቢው ከኢትዮጵያ መባረሩን ተቃወመ

ታትሟል

'ዘ ኢኮኖሚስት' የተባለው መጽሔት ጋዜጣ የኢትዮጵያ ዘጋቢው ፈቃድ መነጠቁን አወገዘ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በኢትዮጵያ የ'ዘ ኢኮኖሚስት' መጽሔት ዘጋቢ የሆነውን ቶም ጋርድነር ፈቃድ መሰረዙን ግንቦት 05/2014 ዓ.ም ማስታወቁ ይታወሳል።

ዘ ኢኮኖሚስት ዛሬ ግንቦት 08/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ ጋዜጠኛውን በተመለከተ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የተሰጠውን ፍረጃም ኮንኗል።

ባለሥልጣኑ የዘጋቢው ፈቃድ እንዲሰረዝ የወሰነው "የሙያ ሥነ ምግባርና የአገሪቱን ሕግና መመሪያ በመጣሱ" መሆኑን ገልጾ ነበር።

መጽሔቱ በምላሹ "ቶም ጋርድነር ድንቅ ጋዜጠኛ ነው። የጋዜጠኝነትን ሥነ ምግባርም ያከብራል" ብሏል።

አክሎም "የትግራይን ጦርነት ጨምሮ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዘገባው ሙያዊ፣ ሚዛናዊና ድፍረት የተሞላው ነው" ሲል ጋዜጣው አቋሙን ገልጿል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ውሳኔውን ከማሳለፉ በፊት ከዘጋቢው ቶም ጋርድነር ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ማድረጉን ገልጾ፣ ከሳምንታት በፊትም ለጋዜጠኛው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉን አስታውቋል።

ጋዜጠኛው በግል የማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የህወሓት መሪ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በስልክ ተወያይተዋል የሚል መልዕክት ማስፈሩን ተከትሎ ባለሥልጣኑ በሪፖርቱ ላይ በተለይም በብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስጠንቅቋል።

ዘ ኢኮኖሚስት በምላሹ፣ የዘጋቢው ፈቃድ የተሰረዘው "በኢትዮጵያ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ነጻት እየተሸረሸረ በመጣበት" ጊዜ ነው ብሏል።

የኒው ዮርክ ታይምስ ዘጋቢ በተመሳሳይ ሁኔታ ፈቃዱን መነጠቁን እና ቢያንስ ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች መታሰራቸውን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ መግለጹን በመጥቀስም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን ውሳኔ ተችቷል።

ቶም ጋርድነት ፈቃዱ መሰረዙን በ48 ሰዓታት ውስጥ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ መታዘዙን መጽሔቱ ጨምሮ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሽልማት ሲሰጣቸው የመገናኛ ብዙኃን አፈናን እንደሚያስቀሩ ቃል መግባታቸውን በመጥቀስ ዘ ኢኮኖሚስት "የኢትዮጵያ መንግሥት ለራሱ ያስቀመጠውን ልኬት እንዲጠብቅ እንጠይቃለን" ብሏል።