ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ሚስጥሬን ለሰሜን ኮሪያ አሳልፈው ሰጥተዋል ያለቻቸውን በቁጥጥር ሥር አዋለች

የደቡብ ኮሪያ ጦር አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የደቡብ ኮሪያ ጦር አባላት
ታትሟል

የደቡብ ኮሪያ ፖሊስ የአገሪቱን ጦር ሚስጥር የሰሜን ኮሪያ ሰላይ ነው ተብሎ ለሚጠረጠር ግለሰብ አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል ሁለት ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ።

ሁለቱ ግለሰቦች የደቡብ ኮሪያ ጥምር ጦር ማዘዣ የይለፍ ቃል አሳልፈው ሰጥተው፣ በምትኩ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተቀብለዋል ብሏል ፖሊስ።

ከእአአ 1950-1953 ከተካሄደው የሁለቱ ኮሪያዎች ጦርነት በኋላ ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ውጥረት የነገሰበት ግንኙነት ውስጥ ይገኛሉ።

የደቡብ ኮሪያ ፖሊስ በሥራ ላይ የነበረ ፖሊስ እና ሲቪል በመጣመር ወታደራዊ ሚስጥሮችን አሳልፈው ሲሰጡ ሲደረስባቸው ይህ የመጀመሪያው ነው ብሏል።

ካሜራ የተገጠመለት ሰዓት እና መረጃ ማከማቻ ፍላሽ ዲስክ ወታደራዊ መረጃዎቹን አሳልፎ ለመስጠት ጥቅም ላይ ውለዋል ተብሏል።

የአገሪቱን ጦር መረጃ አሳልፎ በመስጠት የተጠረጠሩት ሁለቱ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሲሆን የሰሜን ኮሪያ ሰላይ ነው ተብሎ የተጠርጠረው ሰው ማንነት እና መገኛን ፖሊስ አላሳወቀም።

ሚስጥራዊ መረጃውን አሳልፎ ሰጥቷል የተባለው የደቡብ ኮሪያ ፖሊስ አባል ካፒቴን ቢ እንደሚባል እና ከፖሊስ አባሉ ጋር ተባባሪ ነው የተባለው ሲቪል ደግሞ ሊ በሚል መጠሪያ በፖሊስ ዶሴ ላይ ሰፍሯል።

ፖሊስ እንደሚለው በክሪፕቶ ከረንሲ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ሲቪል፣ የፖሊስ አባል በመመልመል ወታደራዊ ሚስጥር አሳልፎ እንዲሰጥ በሰሜን ኮሪያው ሰላይ ጥያቄ የቀረበለት ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ነበር።

ሊ በሚል መጠሪያ የተጠራው ግለሰብም ካፒቴን ቢ የተሰኘውን የፖሊስ አባል ለሚያመጣው መረጃ በቢትኮይን አማካኝነት ክፍያ ለመፈጸም በመስማማት ለሶስት ወራት የደቡብ ኮሪያ ጦር መረጃዎችን አሳልፈው ሰጥተዋል።

በሰሜን ኮሪያው ሰላይ እጅ ምን አይነት መረጃዎች እንደገቡ እስካሁን ግልጽ አይደለም ተብሏል።

መረጃውን አሳልፎ የሰጠው የፖሊስ አባል ወደ 38ሺህ ዶላር ገደማ የሚያወጣ ቢትኮይን ተከፍሎታል። ሊ ደግሞ ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ በክሪፕቶ ከረንሲ ተከፍሎታል።