ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሱዳን የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ ሰላም አስከባሪዎች ወደ ኢትዮጵያ አንመለስም አሉ
በሱዳን የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ አንመለስም ማለታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘገበ።
እንደ ዘገባው ከሆነ የሰላም አስከባሪዎቹ ለመመለስ ፍቃደኛ ያልሆኑት ለደህንነታቸው በመስጋት ነው።
እነዚህ የሰላም አስከባሪዎች ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ትገባኛለች በሚሏት የአብዬ ግዛትም ተሰማርተው የነበሩ ናቸው።
ኢትዮጵያና በሱዳን በግዛት የይገባኛል ጥያቄ እንዲሁም ከህዳሴ ግድብ ሙሌት ጋር ተያይዞ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያት ግንኙነታቸው በመሻከሩ የተነሳ በአብዬ የነበረው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በመድብለ ብሄራዊ ኃይል እንዲተካ ሆኗል።
በሱዳን ተሰማርተው ከነበሩት ኢትዮጵያውያን ሰላም አስከባሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ መመለሳቸውን እና ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑት ደግሞ በሱዳን ጥገኝነት መጠየቃቸውን ኤኤፍፒ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃለ አቀባይ ሰምቻለሁ ሲል ዘግቧል።
ከትግራይ ተወላጅ የሰላም አስከባሪዎች መካከል አንዱ እንደተናገረው ከ500 በላይ ባልደረቦቹ ጥገኝነት እየጠየቁ ነው ብሏል።
በትግራይ ለ18 ወራት በዘለቀው ጦርነት ጦርነት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ በሰላም እንደማይመለሱም አስረድቷል።
በአብዬ ግዛት በተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከግዛቲቷ እንዲወጣ ሱዳን መጠየቋን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስማማቱን ባለፈው ዓመት ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ሱዳን ባወጣችው መግለጫ የኢትዮጵያ ጦር በሌሎች ተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲተካ መስማማታቸውን ብትገልጽም ከየትኛው አገራት እንደሆነ አልተጠቀሰም።
በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ከአብዬ ግዛት እንዲወጡና በሌላ አገር ጦር እንዲተኩ ሱዳን ተመድን በተደጋጋሚ መጠየቋ ይታወሳል።
በተፈጥሮ ሀብት በታደለችው የአቢዬ ግዛት የመንግሥታቱ ድርጅት ያሰማራቸው ሰላም አስከባሪዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው።
በዚህ ኃይል ውስጥ በአጠቃላይ 4,190 ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ሰላም አስከባሪዎች የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 3 ሺህ 158 ወታደሮችና ሰባት የፖሊስ መኮንኖች ከኢትዮጵያ መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
በወቅቱ የሱዳን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ "የኢትዮጵያ ሠራዊት በምሥራቃዊ የሱዳን ድንበር አካባቢ እየተጠናከረ ባለበት ጊዜ ስትራቴጂክ በሆነው የሱዳን ማዕከላዊ ስፍራ ላይ የኢትዮጵያ ኃይሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ምክንያታዊ አይሆንም" ብሎ ነበር።
ባለፈው አመት በሱዳን ዳርፉር ክልል ውስጥ የተሰማራው ሌላ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ቡድንም ኢትዮጵያ ቢመለሱ እንግልት ይደርስብናል በሚል ስጋት ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆነም።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል።
አስራ ስምንት ወራት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ያወጁ ሲሆን ይህም ለሰላም በር ሊከፈትና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት ወደሚያስችል ውይይት መሄድ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።