የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝደንት ምዋይ ኪባኪ አረፉ

ምዋይ ኪባኪ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝደንት ምዋይ ኪባኪ
ታትሟል

የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝደንት ምዋይ ኪባኪ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

የኬንያ ሪፐብሊክ ሦስተኛው ፕሬዝደንት የነበሩት ኪባኪ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ያስታወቁት ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ናቸው።

ፕሬዝደንት ኬንያታ ከቤተ መንግሥታቸው ለኬንያ ሕዝብ በተላለፈ የቀጥታ ሥርጭት ንግግራቸው በቀድሞው ፕሬዝደንት ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።

ኡሁሩ ኬንያታ የቀድሞው ፕሬዝደንት በሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ኬንያ ዘላቂ የሆነ ምጣኔ ሃብት እንዲኖራት አድርገዋል ሲሉ አሞግሰዋል።

ኪባኪ ምስራቅ አፍሪካዊቷን አገር ኬንያን እአአ ከ2002 እስከ 2012 ድረስ መርተዋል።

ፕሬዝደንት ኬንያታ የቀድሞ ፕሬዝደንቱ ሥርዓተ ቀብር እስኪፈጸም ድረስ ብሔራዊ ሐዘን ያወጁ ሲሆን፣ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማም ዝቅ ብሎ ይውለበለባል ብለዋል።

ኡሁሩ ኬንያታ ለቀድሞ ፕሬዝደንቱ ብሔራዊ ሥርዓት ቀብር እንደሚፈጸምም ተናግረዋል።