ዛሬ ከ100 በላይ ሕጻናት ከሳኡዲ ወደ ኢትዮጵያ ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Women and Social Affairs
ዛሬ 101 ሕጻናት ከሳኡዲ አረቢያ ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የሴቶች እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ዜጎችን ከሳኡዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳዑዲ አረቢያ መመለስ የሚፈልጉ ከ35ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን መመዝገቡን አስታውቆ ነበር።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ "ከ35ሺህ በላይ ዜጎች ለመመለስ ተመዝገበዋል፤ በቅርብ ጊዜም ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ" ብለው ነበር።
የሴቶች እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎችን ከሳኡዲ አረቢያ የመመለሱ ሥራ ከተጀመረ 11ኛ ቀኑን እንደያዘ የገለጸ ሲሆን እስካሁን ከ4900 በላይ ዜጎችን ለመመለስ ተችሏል ብሏል።
ሕጋዊ የጉዞ እና የመኖሪያ ፍቃድ የላቸውም የተባሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ በሳኡዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ ይማቅቃሉ።
መንግሥት በ11 ወራት ውስጥ 100ሺህ ኢትዮጵያውያንን ከሳኡዲ አረቢያ ለመመለስ እንደሚሰራ አስታውቋል።
መንግሥት በጊዜያዊነት የሳኡዲ ተመላሾች የሚያርፉበት መጠለያ እና የሕክምና አገልግሎት እየቀረበላቸው ሲሆን ቢሆንም በዘላቂነት እራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉበት ሁኔታን በተመለከተ እቅድ ስለመኖሩ እርግጥ አይደለም።
ከሁለት ወራት ገደማ በፊት በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የሚመር ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ወደ ሳውዑ አረቢያ ተጉዞ በእሰረኞች አያያዝ እና ወደ አገር ቤት በሚመለሱበት ጉዳይ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገሩን ይታወሳል።
ባለፉት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና ሥራ አጥነት፣ ድርቅ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕገ-ወጥ እና አደገኛ በሆኑ የባሕር መስመሮች በኩል በየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲገቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ደግሞ በባሕር እና በበረሃዎች ላይ በሚያደርጓቸው ጉዞዎች ወቅት በሚገጥሟቸው አደጋዎች ምክንያት ለህልፈት መዳረጋቸው በተደጋጋሚ ተዘግቧል።












