ተመራማሪዎች የ53 ዓመቷን ሴት ቆዳ የ23 ዓመት የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ሠሩ

የፎቶው ባለመብት, FÁTIMA SANTOS
የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶች የ53 ዓመቷን ሴት ቆዳ የ23 ዓመት እንዲመስል አድርገው መሥራት ችለዋል።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ይህንን ፀረ ዕድሜ ግኝት ለሌሎችም የሰውነት ክፍሎች ማድረግ ይቻላል።
የዚህ ጥናት ዓላማ ከዕድሜ መግፋት ጋር ለሚመጡ እንደ የስኳር በሽታ፣ የልብ በሽታና የነርቭ ችግሮች መፍትሔ ማፈላለግ ነው።
ከ25 ዓመታት በፊት ዶሊ የተባለችውን በግ የፈጠረው ቴክኖሎጂ ነው ያረጀ ቆዳን የወጣት ያስመሰለው።
የካምብሪጁ ባብራሃም ተቋም የጥናት ቡድን መሪ ፕሮፌሰር ዎልፍ ሪክ ናቸው።
ይህ ግኝት ሰዎች ቢያረጁ በሽታ ሳያገኛቸው ጤናማ ሆነው እንዲቆዩ ድጋፍ ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ይገልጣሉ።
"ስለዚህ ጉዳይ ስናልም ነው የኖርነው። በርካታ በሽታዎች ከዕድሜ መግፋት ጋር እየባሱ ይሄዳሉ፤ ታድወያ ሰዎችን ከዚህ ሰቀቀን መገላለግ ያስደስታል" ይላሉ።
ነገር ግን ይላሉ ፕሮፌሰሩ፤ ጥናቱ ገና ጅምር እና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው ይላሉ።
ይህ ግኝት ከቤተ-ሙከራ ወጥቶ ወደ ክሊኒክ ከመሄዱ በፊት ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ ይጠበቅበታል።
ቢሆንም የቆዳ ዕድሜን ቀንሶ ማየት ትልቅ ድል እንደሆነ ፕሮፌሰሩ አይክዱም።
የዚህ የተሸበሸበ ቆዳን መልሶ ወጣት የማድረግ ግኝት መላ ከ1990ዎቹ አንድ ጥናት የተመዘዘው ነው።
በወቅቱ የኤደንብራ አጥኚዎች የቆዳ ሴል ወስደው ወደ ሽል ቀይረውት ዶሊ ብለው የጠሯትን በግ ፈጥረው ነበር።
አጥኚዎቹ በጊዜው ዓላማቸው የቤተ-ሙከራ በግ አሊያም ሰው መፍጠር አልነበረም፤ ለሰው ልጅ የሚሆን ኢምብሮይክ ስቴም የተባለ ሴል መፍጠር እንጂ።
ይህን ሴል ለውጥ ለሚያስፈልጋቸው የሰውነታችን ክፍሎች መቀየሪያ ማዋል ይችላሉ።
ዶሊ የተፈጠረችበት መንገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።
የፕሮፌሰር ሪክ ቡድን የመጨረሻውን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ነው የ53 ዓመት ዕድሜ ያለውን ቆዳ የ23 ማስመሰል የቻሉት።
"ለመጀመሪያ ጊዜ ጥናት ስናደርግበት የነበረው ቆዳ በ30 ዓመታት ወጣት መሆኑን ስሰማ የተሰማኝን ደስታ መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር" ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
ጥናቱ አሁኑኑ ወደ ሥራ የማይገባው አሁን ባለበት ደረጃ ተግባራዊ ቢደረግ በካንሰር የመያዝ ዕድልን ስለሚጨምር ነው።
ነገር ግን ቆዳን እንዲህ አሳምሮ ወጣት ማድረግ እንደሚቻል ከታወቀ የጎንዮሽ ጉዳቱ ዝቅ ያለ መላ መፈለግ አያዳግትም።
"ዓላማችን ሰዎች ዕድሜያቸው እንዲጨምር ማድረግ አይደለም፤ ቀሪ ዘመናቸውን ጤናማ ሆነው እንዲኖሩ ማድረግ እንጂ። ሰዎች ጤናማ ሆነው ማርጀት ይችላሉ" ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
አልፎም ሰዎች በአደጋ ምክንያት ቆዳቸው ጉዳት ሲደርስበት አዲሱ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል አጥኚው ይጠቁማሉ።
ቀጣዩ እርምጃ ይህ ቴክኖሎጂ ልክ እነጡንቻ፣ ጉበትና የደም ሴል ላይ ሊሠራ ይችላል ወይ የሚለውን ማጥናት ነው።
የዘርፉ ሰዎች የዚህ ቴክኖሎጂ ውጤት ገበያ ላይ ወጥቶ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ይላሉ።
ይህ አዲስ ግኝት ሙሉ የሰውነት ክፍልን እንዳያረጅ ማድረግ አሊያም የማያስረጅ ክኒና ወደ መፍጠር ይወስደን ይሆን የሚለው ጥያቄ አሁን ምላሽ ሊያገኝ ይችላል ይላሉ ፕሮፌሰሩ።












