የምክር ቤቱ የመገናኛ ብዙኃን የቦርድ አባላት ሹመት ጥያቄ አስነሳ

የፎቶው ባለመብት, HPR
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የቦርድ አባላት ሹመት ጥያቄ አስነሳ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት መጋቢት 29/2014 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን 9 የቦርድ አባላትን በአብላጫ ድምፅ አፀድቋል።
ምክር ቤቱ ሹመቱን ካጸደቀላቸው ግለሰቦች መካከል፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባሏ ዶ/ር አጋረደች ጀማነህ ይገኙበታል።
ታዲያ በርካቶች ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን ለማቋቋም ያወጣው አዋጅ ቁጥር 1238/2013 በመጣስ ከሕግ ውጪ ሹመት ሰጥቷል በማለት እየተከራከሩ ነው።
ከእነዚህ መከራከሪያ ነጥቦች መካከል አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ በቦርድ አባልነት መካተት እና የቦርድ አባላት ተዋጽኦ ውስን ነው የሚሉት ይገኙበታል።
የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሠረት ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት ከሚመረጡባቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ፤ የፖለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆን አልያም በፖለቲካ ፓርቲ ያልተቀጠረ የሚለው ይገኝበታል።
ይሁን እንጂ ትናንት ምክር ቤቱ ካጸደቃቸው የቦርድ አባላት መካከል የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባል ይገኙበታል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ, 1
የቦርድ አባላቱን ሹመትን በተመለከተ ሌላኛው መከራከሪያ ጉዳይ የቦርድ አባላት እጩዎች ምልመላ እና የማጽደቅ ሂደት ግልጽ አልነበረም የሚለው ነው።
የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 የባለስልጣኑ የቦርድ በአላት እጩዎች የመመልመል እና የማጸደቁ ሂደት ለሕዝብ ግልጸ በሆነ መልኩ መካሄድ አለበት ይላል።
አንቀጽ 9.2 ሕዝቡ የቦርድ አባላት እጩዎችን እንዲጠቁም እና በእጩ አባላት ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ይደነግጋል።
ከዚህ በተጨማሪም የእጩዎች አመራርጥ ሂደት እና የእጩዎች ዝርዝር ቀድሞ በመገናኛ ብዙሃን ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት ይላል አዋጁ።
ታዲያ በርካቶች ይህ የእጩ ቦርድ አባላት ምልመላ እና የማጽደቅ ሂደት ግልጽ ስለመሆኑ ጥያቄዎችን እያነሱ ይገኛሉ።
የቦርድ አባላት ሹመት ሂደት ላይ ጥያቄ ያስነሳው ሌላኛው ጉዳይ፤ የቦርድ አባላቱ ተዋጽኦን ይመለከታል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ, 2
አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 9.5 ከቦርዱ አባላት መካከል፤ ሁለቱ ከሲቪል ማሕብረሰብ፣ ሁለቱ ከመገናኛ ብዙሃን፣ሁለቱ ለመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ጠቀሜታ እና አግባብነት ካላቸው የተለያዩ ተቋማና የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ሦስቱ አግባብነት ካላቸው የመንግሥት አካላት የተወጣጡ መሆን አለባቸው ይላል።
ይሁን እንጂ ሹመታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቁ 9 አባላት ውስጥ ከመገናኛ ብዙሃን የተወከለ አለመኖሩ ጥያቄ አስነስቷል።
የቦርድ አባላት ኃላፊነታቸው ምንድን ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራቸውን በተገቢው መንገድ መፈጸም የሚችሉ ከዘርፉ ጋር የተገናኘ የትምህርት ዝግጅት እና ብቃት ያላቸውን እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 የተቀመጡ መስፈርቶችን የሚያሟሉ 9 የቦርድ አባላት አቅርበው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስሾማሉ።
የቦርድ አባላቱ የመጀመሪያው ኃላፊነት የአዋጅ ቁጥር 1238/2013 አፈጻጸም እና የባለስልጣኑን ሥራዎች በበላይነት መቆጣጠር ነው።
ቦርዱ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን የሥራ እቅድ፣ በጀት እና የሥራ እንቅስቃሴ ይገመግማል፤ የባለስልጣኑን የሠራተኞች ቅጥር እና አስተዳደር መመሪያ ያወጣል እንዲሁም የባለስልጣኑን ዋና ዳይሬክተር በመመልመል ለመንግሥት አቅርቦ ያሰይማል የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
















