ዊል ስሚዝ ከትልቁ የሽልማት ተቋም ራሱን አገለለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካዊው ተዋናይ ዊል ስሚዝ በግዙፉ የሽልማት መድረክ ላይ ኮሜዲያን ክሪስ ሮክን በጥፊ ካጋጨ በኋላ ራሱን ከሽልማት ተቋሙ አገለለ።
"በ94ኛው የኦስካርስ ሽልማት ወቅት ያደረግኩት ነገር አስደንቃጭ እና ይቅርታ የማይደረግለት ነው" ነው የሚል መግለጫ አውጥቷል።
አካዳሚው የዊል ስሚዝን የመልቀቂያ ደብዳቤ መቀበሉን ገልጦ የዲስፕሊን ቅጣት ለማድረግ እያሰበ መሆኑን አስታውቋል።
ኮሜዲያኑ ክሪስ ሮክ አሎፔሺያ የተሰኘው ፀጉር የሚያሳጣ በሽታ ባለባት ጄዳ ፒንኬት ስሚዝ ላይ መቀለዱን ተከትሎ ነው ከዊል ስሚዝ ጥፊ የቀመሰው።
ዊል ስሚዝ ድምፁ አዳራሹን ያዳረሰ ጥፊ የሙያ አጋሩ ላይ ካሳረፈ ከደቂቃዎች በኋላ የዓመቱ ምርት ተዋናይ ተብሎ ተሸልሟል።
"በዚህ ድርጊቱ ያሳዘንኳቸው ሰዎች ብዙ ናቸው። ክሪስ ሮክና ቤተሰቦቹን ጨምሮ ውድ ጓደኞቼንና ወዳጆቼን፤ ታዳሚውንና ተመልካቹን አስከፍቻለሁ" ሲል ዊል ስሚዝ ባለፈው አርብ ኦፊሴላዊ ይቅርታ ጠይቆ ነበር።
"አካዳሚው በኔ የነበረውን እምነት በመሻሬ፤ ሌሎች ዕጩዎችና አሸናፊዎች ድላቸውን እንዳያከብሩ በማድረጌ ልቤ ተሰብሯል።"
ኦስካር የተሰኘውን ግዙፍ የፊልም ሽልማት የሚያዘጋጀው አካዳሚ ኦፍ ሞሽን ፒክቸር አርትስ ኤንድ ሳይንስስ ከ10 ሺህ በላይ አባላት አሉት።
የዚህ ድርጅት አባል ለመሆን ማመልከቻ ማስገባት ምንም ዋጋ የለውም። ባይሆን ቢያንስ ከሁለት የድርጅቱ አባላት እውቅና ማግኘት ያስፈልጋል።
ነገር ግን በሥራቸው ለኦስካር የታጩ ሰዎች በቀጥታ የድርጅቱ አባል ይሆናሉ።
ዊል ስሚዝ "ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው በሥራቸው ላሸነፉ ሰዎች ነው" ብሏል በመግለጫው።
"ለውጥ ጊዜ ይፈጃል። እኔም አመክንዮን አመፅ እንዳይቀማኝ ለማድረግ ቆርጩ እሠራለሁ" ሲል መግለጫውን ዘግቷል።
የአካዳሚው ፕሬዝደንት ዴቪድ ሩቢን የዊል ስሚዝን መልቀቂያ መቀበላቸውን ገልጠው እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ክሪስ ሮክ ቦስተን ከተማ በነበረው የስታንድ አፕ ኮሜዲ ሥራው ወቅት "ነገሩን እስካሁን እያብላላሁ ነው" ሲል ለታዳሚው ተናግሯል።
የ57 ዓመቱ ኮሜዲያን ክሪስ ሮክ በአሜሪካ ከተሞች እየዞረ ሥራውን ለአድናቂዎቹ እያቀረበ ይገኛል።
ዊል ስሚዝ ላይ ክስ እንደማይመሠርት አስታውቋል የተባለው ክሪስ ሮክ የኮሜዲ ሥራውን በሚያቀርብበት ወቅት ከአድናቂዎቹ ደመቅ ያለ ጭብጨባ ተበርክቶለታል።
የዊል ስሚዝ ባለቤት ጄዳ ፒንኬት ስሚዝ ባለፈው ረቡዕ ኢንስታግሯም ገጿ ላይ "አሁን ጊዜው የድኅነት ነው፤ እኔም ተዘጋጅቻለሁ" ስትል ፅፋለች።












