ዊል ስሚዝ ከአዳራሹ በግድ እንዲወጣ ክሪስ ሮክ አለመፈለጉን የኦስካር ሽልማት አዘጋጅ ገለጸ

የኦስካር ሽልማት አዘጋጁ ዊል ፓከርና ክሪስ ሮክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኦስካር ሽልማት አዘጋጁ ዊል ፓከርና ክሪስ ሮክ
ታትሟል

ክሪስ ሮክን በመድረክ ላይ በጥፊ ከተማታ በኋላ ከአዳራሹ በግድ እንዲወጣ ለማድረግታቅዶ የነበረ ቢሆንም ክሪስ ሮክ ይህ እንዲሆን አለመፈለጉን የኦስካር ሽልማት አዘጋጅ ገልጿል።

ዊል ስሚዝ በባለቤቱ ጄዳ ፒንኬት ላይ የቀለደውን ክሪስ ሮክን በጥፊ ከተማታ በኋላ የኦስካር አካዳሚ ከፍተኛ ኃላፊዎች ተዋናዩን በግድ ሊያስወጡት እንደነበር መስማቱን አዘጋጁ ዊል ፓከር ተናግሯል።

ዊል ፓከር በእነዚህ ውይይቶች ላይ ተሳታፊ ባይሆንም በቦታው ላይ ለነበሩት አመራሮች ክሪስ ሮክ ይህንን አይፈልግም በማለት መናገሩን አስረድቷል።

ዊል ፓከር ከክስተቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረገው ቃለ ምልልስ ለከፍተኛ ኃላፊዎቹ "ክሪስ ሮክ ያለውን መጥፎ ሁኔታ ማባባስ እንደማይፈልግ በግልፅ ተናግሯል" ሲሉ መናገሩን ከኤቢሲ ጉድ ሞርኒንግ ጋር ባደረገው ቆይታ አስረድቷል።

አክሎም "ክሪስ የነበረበት ስሜት ይህ ነበር። ምንም በቀል የመፈለግ ሁኔታም አልታየበትም። ንዴትም አልተነበበትም" ብሏል።

"ስለዚህ እኔ በዚያን ጊዜ ክሪስ ሮክ የሚፈልገውን ነገር አሳውቄያቸዋለሁ። ምክንያቱም በወቅቱ ዊል ስሚዝን በግድ ማስወጣት ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ስለተገለጸልኝ" ብለዋል።

"ዊል ስሚዝ በፍቃደኝነት እንዲወጣ መጠየቁንና እኔ ባልተሳተፍኩበት ውይይት እንደነበር ተብራርቶልኛል" በማለት አስረድቷል።

ፓከር አክሎም ክሪስ ሮክ በስነ ስርዓቱ ላይ ለፖሊሶች ዊል ስሚዝ እንዲታሰር እንደማይፈልግ መናገሩንም ገልጿል።

"ፖሊሶቹ በወቅት ጥቃት ተፈፅሟል የሚል ቃል ነው የተጠቀሙት። ተዘጋጅተናል፤ ክሰስ በቁጥጥር ስር እናውለዋለን ብለውት ነበር" ብሏል።

"ፖሊሶቹ ያለውን አማራጭ እየዘረዘሩለት ነበር። ክሪስ ግን ሊያስጨርሳቸውም ፈቃደኛ አልነበረም። ደህና ነኝ ብሎ አጣጣለ። መሃል ላይ ገብቼ እስቲ ይጨርሱ ሁሉ ብያለሁ" በማለት አስረድቷል።

"ሌሎች እንዲሁ የሎስ አንጀለስ ፖሊሶችም በተመሳሳይ ያሉትን አማራጮች አስረድተው፤ እርምጃ እንድንወስድ ትፈልጋለህ ወይ? ሲሉት በጭራሽ የሚል መልስ ነው የሰጣቸው" ብሏል።

ዊል ስሚዝ ባለቤቱ ጄዳ አሎፔሺያ በተባለ የጸጉር መነቃቀል ምክንያት መላጣ መሆኗን አስመልክቶ ክሪስ ሮክ በመቀለዱ በጥፊ የመታው ሲሆን የኦስካር ሽልማት አዘጋጆች ምንም ባለማድረጋቸውም ትችት እየቀረበባቸው ነው።