የግዙፉ አማዞን ሠራተኞች አሜሪካ ውስጥ የመጀመሪያውን ማሕበር መሠረቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የግዙፉ ቴክኖሎጂ ኩባንያ አማዞን ሠራተኞች አሜሪካ ውስጥ እውቅና ያለው ማሕበር በመመሥረት ታሪክ ፅፈዋል።
ከግማሽ በላይ ኒውዮርክ የሚገኘው የድርጅቱ መጋዘን ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የአማዞን ሠራተኞች ማሕበርን ለማቋቋም ተስማምተው ድምፅ ሰጥተዋል።
ይህን አብዮት የመራው የቀድሞ የድርጅቱ ሠራተኛ የሆነውና ግዙፉ አማዞን ለሠራተኞቹ ደኅንነት ደንታ የለውም በማለት ሲሞግት የነበረው ክሪስ ስሞልስ ነው።
የክሪስ ስሞልስ ድል ለዘመናት ሠራተኞች ማሕበር እንዳይመሠርቱ ሲታገል ለነበረው አማዞን ሽንፈት ሆኗል።
ነገር ግን አላባማ ውስጥ በተመሳሳይ ማሕበር ለመመሥረት ጥረት እያደረጉ የነበሩ የአማዞን ሠራተኞች ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
አማዞን አሜሪካ ውስጥ በርካታ ሠራተኞች ካሏቸው ድርጅቶች መካከል ሁለተኛው ነው።
ክሪስ ስሞልስ ከችሎት ሲወጣ ድካም የተጫጫነው ቢመስልም የድል ብርሃን ፊቱ ላይ ይበራል። ደስታውን የተጋሩ የድርጅቱ ሠራተኞች ቻምፖኝ ከፍተው ተራጭተዋል።
"ማሕበሩ እንዳይቋቋም ለማድረግ የተደረገውን ጥረት ለመርታት ብዙ ጥረት አድርገናል" ሲል ለተሰበሰበው ሰው ተናግሯል።
የማሕበሩን መቋቋም አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው አማዞን በኒውዮርክ ሽንፈት እንደተበሳጨ አልካደም።
ወደፊት እንዴት እንደምንቀጥል እየገመገምኩ ነው፤ አልፎም ያለአግባብ ድምፅ እንዲመጣ ያደረጉትን እመረምራለሁ ብሏል ድርጅቱ።
"ሠራተኞች ከድርጅቱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ቢኖራቸው ይጠቀሙ ነበር" ይላል የግዙፉ ድርጅት መግለጫ።
የሩትገርስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሬቤካ ጊቫን የክሪስ ስሞልስን ድል "የዳዊትና ጎሊያድ" ታሪክ ሲሉ ይገልጡታል።
ነገር ግን ገና ብዙ ትግል ከዓለማችን ቱጃሩ ግለሰብ ድርጅት እንደሚጠብቀው ፕሮፌሰሯ ይናገራሉ።
"አማዞን ይህንን ድል ለመቀልበስ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ማሕበሩን ለማፈራረስ ብዙ ጉድጓድ ይቆፍራል። ይህ ድል ለሌሎችም መነሳሳት ስለሆነ።"
ክሪስ ስሞልስና የሠራተኞች አደራጅ ቡድኑ አሁን ማሕበር መሥርተዋል። አማዞን መታገል የሚችል ገለልተኛ የሠራተኞች ማሕበር አቋቁመዋል።
ሰውዬው የቀድሞ የድርጅቱ ሠራተኛ ነው። አማዞን ክሪስን "ብልሃት የሌለው፤ ንግግር የማይችል" ሲል በአንድ ድብቅ ደብዳቤ ወቅሶት ነበር።
የ33 ዓመቱ ክሪስ ለአራት ዓመታት ድርጅቱን ካገለገለ በኋላ በፈረንጆቹ 2020 የኮሮናቫይረስ ሕግጋት እየተጣሱ ነው ብሎ በመቃወሙ ነበር የተባረረው።
ነገር ግን እንደ ክሪስ ተሰብስበው ለሚጠብቁት ሠራተኞች "ነገር ግን ይህ ድል ከዚህም በላይ ነው።"
አማዞን አሜሪካ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሠራተኞች አሉት። ድርጅቱ ጥብቅ የሆነ አመራር በሠራተኞች ላይ በማራመድ ይታወቃል።
አማዞን ከምሥረታው ጀምሮ ሠራተኞች ማሕበር እንዳይመሠርቱ ሲታገል ቆይቷል።
ነገር ግን ይህ ድል ሌሎችም የድርጅቱ ሠራተኞች ማሕበር እንዲመሠርቱ ማነሳሻ ይሆናል ሲሉ ተሟጋቾች ተስፋ ያደርጋሉ።
አማዞን የመጋዘን ፍጥነትን ያደናቅፋሉ ያላቸውን ማሕበራት እንዳይቋቋሙ ለማድረግ ብዙ መንገድ ተጉዟል።
ሹመኞች ድርጅቱ ጥሩ የሚባል ደሞዝና ጥቅማጥቅም ስላለው ሠራተኞች ቀጥታ ግንኙነታቸው ከኛ ጋር ቢሆን መልካም ነው ሲሉ ይሞግታሉ።
የኒውዮርኩን ማሕበር ለመመሥረት በነበረው ስብሰባ ላይ ሹመኞቹ የማሕበሩ መሪ የሥራ ስምምነትን [ኮንትራክት] ለማድረግ አቅም የለውም ሲሉ ተከራክረዋል።
አማዞን የኒውዮርክ ማሕበር የተቋቋመው ብሔራዊው የሠራተኞች ግንኙነት ቦርድ ክስ እመሠርታለሁ ባለ ጊዜ ስለሆነ ይግባኝ እጠይቃለሁ ብሏል።
ከ4 ሺህ በላይ ሠራተኞች የኒው ዮርኩን ማሕበር ለማቋቋም ድምፃቸውን ሰጥተዋል። ከነዚህ መካከል 2654 ሰዎች ማሕበሩን ለመመሥረት ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
ክሪስ፤ ድርጅቱ የተሻለ ክፍያ ሊከፍል፤ የጤና መድኅን ሊሰጥ፤ ማግለል ሊያቆምና የእረፍት ቀናትን ሊያሻሽል ይገባል ሲል የአማዞን ሠራተኞች ማሕበርን ያቋቋመው ባለፈው ዓመት ነበር።
አሜሪካ ውስጥ 6.1 በመቶ ብቻ የግል መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የሠራተኛ ማሕበራት አባል ናቸው።












