ሩሲያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያንን አስገድዳ ወደ ግዛቷ ማስገባቷ ተነገረ

ታትሟል

የሩሲያ ጦር በሺዎች የሚቆጠሩ የማሪዩፖል ከተማ ነዋሪዎችን አስገድዶ ወደ ግዛቱ ወሰዷል ሲል የዩክሬን መንግሥት አስታወቀ።

የሳተላይት ምስሎች እንዳረጋገጡት ሩሲያ በግዛቷ ውስጥ በሚገኝ እና ቤዚሜኔ ተብሎ በሚጠራ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ከ5ሺህ የማያንሱ ዩክሬናውያንን ይዛ ትገኛለች።

የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አርያና ቬሬሸቸከ የሩሲያ ጦር 40ሺህ የዩክሬን ዜጎችን ወደ ድንበሩ ወስዷል ብለዋል።

ከዩክሬኗ ማሪዩፖል ተፈናቅሎ አሁን በሩሲያ የሚገኝ አንድ ዩክሬናዊ፤ "ሁላችንም በኃይል ነው የተወሰድነው" በማለት ተናግሯል።

ተዋጊ ኃይል ንጹሃን ዜጎችን በኃይል ወደ ድንበሩ ማሸጋገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተደርጎ ይወሰዳል።

በአሁኑ ወቅት በሩሲያ ጦር ከፍተኛ ድበደባ እየደረሰባት በምትገኘው ማሪዩፖል ከ170ሺህ በላይ ዜጎች መውጫ አጥተው እንደሚገኙ የከተማዋ አስተዳደር አስታውቋል።

በማሪዩፖል የሚገኙ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃ፣ የምግብ እና የመድኃኒት እጥረት እንዳለባቸውም በስፋት ተዘግቧል።

የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ቃል አቀባይ ማር ሞሪስ ሩሲያ እና ዩክሬን የደኅንነት ማረጋገጫ ሲሰጡ ብቻ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያደርሱ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ንጹሃንን ከግጭት ቀጠና ለማስወጣት የተደረሱ ስምምነቶች በሩሲያ ጦር ተኩስ ምክንያት የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉ በስፋት ተገልጿል።

"ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ማረጋገጫ መስጠት እና ለንጹሃን ደኅንነቱ የተረጋገጠ መተላለፊያ ማዘጋጀት አለባቸው። መተላለፊያ መንገዶቹን በይፋ መግለጽ እና ሰዎች መውጣት እንዲችሉ ሰፊ ጊዜ መስጠት አለባቸው" ብለዋል የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ቃል አቀባይ ማር ሞሪስ ለቢቢሲ።

የማሪዩፖል ከተማ ነዋሪ የነበረች እና ወደ ሩሲያ በኃይል እንደተሰወደች የምትናገረው አሪና፤ እርሷ እና ሌሎች በማሪዩፖል ከተማ ሳሉ የሩሲያ ወታደሮች "ለራሳችሁ ደኅንንት ሲባል ወደ ሩሲያ መሄድ አላባችሁ አሉን" ትላለች።

ወደ ሩሲያ ድንበር ለ4 ኪሎ ሜትሮች ያክል በእግር ከተጓዙ በኋላ የሩሲያ መንግሥት ደጋፊ በሆኑ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ወደምትገኘው እና ሞስኮ የዶኔስክ ሕዝቦች ሪፐብሊክ ስትል እውቅና ወደሰጠችው ተገንጣይ ክልል እንደተወሰዱ ትገልጻለች።

"እዛ ካደረሱን በኋላ ወደ ሩሲያ ለመሄድ ወይም ዶኔስክ ሪፐብሊክ መቆየት በሚለው ላይ እራሳችን እንድንወስን ያደርጋሉ" ትላለች።

ሮሲስካያ የተባለው የሩሲያ ጋዜጣ ከአንድ ሳምንት በፊት በርካታ ተፈናቃዮችን የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከማሪዩፖል 90 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ቤዚሜኔ መጠለያ ጣቢያ መድረሳቸውን ዘግቦ ነበር።

ምንም እንኳ የዩክሬን ባለሥልጣናት በዚህ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዩክሬናውያን በመድኃኒት እጥረት እየሞቱ ነው ቢሉም፤ በመጠለያ ጣቢያው ለሚገኙት ተፈናቃዮች የሩሲያ መንግሥት ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑ ተዘግቧል።