ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ10 በላይ የኬንያ ወታደሮች በአል-ሸባብ ጥቃት ተገደሉ
በሶማሊያዋ ጌዶ ግዛት ከመንገድ ዳር በተጠመደ ፈንጂ ከ10 በላይ የኬንያ ወታደሮች መገደላቸው ተገለጸ።
ከሞቱት በተጨማሪ አምስት ሰዎች ክፉኛ ለቆሰሉበት ጥቃት ከአል-ቃይዳ ጋር ግነኙነት ያለው አል-ሸባብ ተጠያቂ ተደርጓል።
በጥቃቱ የተገደሉት ወታደሮች ማንነት ይፋ ባይሆንም ለኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሆነው ቀርበው የነበሩ አንድ ፖለቲከኛ ከሟቾቹ መካከል ታናሽ ወንድማቸው እንደሚገኝበት በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ምንም እንኳ ጥቃቱን ያደረሰው አል-ሸባብ ነው ቢባልም ጽንፈኛው ቡድን እስካሁን ኃላፊነቱን ስለመውዱ አልተገለጸም።
ጽንፈኛው ቡድን አል-ሸባብ የሶማሊያ መንግሥትን ከአስር ዓመት በላይ ሲዋጋ ቆይቷል። በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎችም ጠንካራ ይዞታ መሥርቷል።
አል-ሸባብ በሲቪል ሰዎች እና በሶማሊያ በተሰማሩ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ላይ ተመሳሳይ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት በማድረስ የሚታወቅ ነው።
በዚህ ጥቃት የተገደሉት ወታደሮች የሶማሊያ የፌደራል መንግሥት የአል-ሸባብ ታጣቂዎችን ለመዋጋት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ በአገሪቱ የተሰማሩ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ሰው የሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች፣ የመንግሥት ተቋማትን እና የፍተሻና የደኅንነት መቆጣጠሪያ ቦታዎች ላይ የታጣቂዎች ጥቃቶች እየጨመሩ ይገኛል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በልደወይን በተሰኘችው ማዕከላዊ ሶማሊያ ውስጥ በምትገኝ ከተማ ባለሥልጣና በሚያዘወትሩት ምግብ ቤት አንድ አጥፍቶ ጠፊ ባፈነዳው ቦምብ ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
በሶማሊያ የተጓተተው የፓርላማ ምርጫ እስካሁን ያልተከናወነ ሲሆን የጥቃቶቹ መበራከት የፓርላማ አባላት አዲስ ፕሬዝዳንት እንዳይመርጡ ሂደቱን ለማደናቀፍ እየተደረገ ያለ ጥረት ነው ሲሉ ተንታኞች ያስረዳሉ።