ሰሜን ኮሪያ የተኮሰችው ሚሳኤልመክሸፉን ደቡብ ኮሪያ ገለጸች

ሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ የተኮሰችው ምንነቱ በውል ያልታወቀ ተወንጫፊ መክሸፉን ደቡብ ኮሪያ አስታወቀች።

ሰሜን ኮሪያ ለሙከራ ያስወነጨፈችው ሚሳኤል ወዲያው የታሰበለትን ሳያሳካ ከሽፏል ተብሏል።

ይህ ሚሳኤል የተተኮሰው ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ ወጣ ብሎ ካለ አየር ማረፊያ ነው።

ይህ አየር ማረፊያ ሰሜን ኮሪያ ከዚህ ቀደም በርካታ ሚሳኤሎችን ያስወንጨፈችበት እና በቅርቡም የተኮሰችው እና አሜሪካ አህጉር ተሻጋሪ ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ናቸው ያለቻቸው ሙከራዎችም የተደረጉበት ነው።

ይህ ዜና የተሰማው ሰሜን ኮሪያ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የጦር መሳሪያ ሙከራዋን እያጠናከረች በመጣችበት ወቅት ነው።

"ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ከሱናን አካባቢ የማይታወቅ ተወንጫፊ ተኩሳለች። ነገር ግን ወዲያው ከሽፏል ተብሎ ይገመታል" ሲሉ የደቡብ ኮሪያ ጦር አዛዥ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ አህጉር ተሻጋሪ ነው የምትለውን ባለስቲክ ሚሳኤል ጨምሮ በዚህ አመት እስካሁን ዘጠኝ ሙከራዎችን አድርጋለች።

መቀመጫውን በደቡብ ኮሪያ መዲና ያደረገው ኤንኬ ኒውስ፤ ሙከራ ተደርጎበታል ከተባለበት አየር ማረፊያ አቅራቢያ ከፍተኛ ፍንዳታ እና ቃጠሎ ማየታቸውን ነግረውኛል ሲል የዓይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ቢያንስ 5,500 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚምዘገዘጉ አህጉር ተሻጋሪ ሚሳኤሎች አሜሪካ ሊደርሱ የሚችሉ ሲሆን የተሰሩበት መንገድ ደግሞ ኒውክሌር እንዲሸከሙ ተደርገው ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራዎችን እንዳታከናውን የከለከለ ሲሆን ጥብቅ ማዕቀቦችም ተጥለውባታል።

የሰሜን ኮሪያ መሪ ከቀድሞ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር መነጋገራቸውን ተከትሎ ፒዮንግያንግ የረጅም ርቀት የባለስቲክ ሚሳኤሎች እና የኒውክሌር ሙከራዎችን ከማድረግ ተቆጥባ ነበር።

ይሁን እንጂ ኪም እአአ 2020 ላይ አገራቸው የረጅም ርቀት የሚሳኤል ሙከራዎች ወደማድረግ መመለሷን ገልጸዋል።