ለ2013 የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የከፍተኛ ትምህርት የመግቢያ ነጥብ ይፋ ሆነ

ታትሟል

የትምህርት ሚኒስቴር የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተናን በሁለት ዙር ለወሰዱ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ነጥብን ይፋ አደረገ።

ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው በሁለት ዙር ለተሰጠው የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና የተቀመጠው የማለፊያ ነጥብ የተለያየ መሆኑን አስታውቋል።

በዚህም መሰረት በመጀመሪያ ዙር የተሰጠውን ፈተና የወሰዱ የተፈጥሮ ሳይንስ እና የማኅበራዊ ሳይንስ መደበኛ ተማሪዎች ውጤት እንደሚከተለው ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል።

በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ለመማር ለተፈጥሮ ሳይንስ መደበኛ ተፈታኞት የማለፊያ ነጥብ ለወንድ 363 ለሴት 351 ሲሆን በተፈጥሮ ሳይንስ በታዳጊ ክልሎች እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ላሉ መደበኛ ተፈታኞች ለወንድ 351 ለሴት ደግሞ 339 ማለፊያ ነጥብ እንዲሆን ተወስኗል።

በተጨማሪም ለተፈጥሮ ሳይንስ መስማት ለተሳናቸው ሁለቱም ፆታዎች የማለፊያ ነጥብ 300 ሲሆን፣ ለተፈጥሮ ሳይንስ ድጋሚ ተፈታኞች የማለፊያ ነጥብም 380 ሆኗል።

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በመጀመሪያው ዙር የተፈተኑ እና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ለመከታተል የተፈጥሮ ሳይንስ የመግቢያ ነጥብ 300 እንደሆነ ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

ለማኅበራዊ ሳይንስ መደበኛ ተፈታኞች የማለፊያ ነጥብ ለወንድ 264፣ ለሴት 254 እንዲሆን ሲወሰን፣ በማኅበራዊ ሳይንስ በታዳጊ ክልሎች እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ላሉ መደበኛ ተፈታኞች ለወንድ 254፣ ለሴት 250 ማለፊያ ነጥብ ሆኗል።

ለማኅበራዊ ሳይንስ መስማት ለተሳናቸው ሁለቱም ፆታዎች ማለፊያ ነጥብ 250 እና በማኅበራዊ ሳይንስ ድጋሚ ተፈታኞች ለሁለቱም ፆታዎች የማለፊያ ነጥብ 280 እንዲሆን ተወስኗል።

በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ለመከታተል የማኅበራዊ ሳይንስ የመግቢያ ነጥብ 250 ተደርጓል።

በሁለተኛ ዙር ፈተናቸውን ለወሰዱ መደበኛ ተፈታኞች ደግሞ፣ በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ለመማር ለተፈጥሮ ሳይንስ የማለፊያ ነጥብ ለወንድ 423 ለሴት 409 ሲሆን፣ በተፈጥሮ ሳይንስ በታዳጊ ክልሎች እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ላሉ መደበኛ ተፈታኞች ለወንድ 410፣ ለሴት ደግሞ 396 ማለፊያ ነጥብ ሆኗል።

በተጨማሪ ለተፈጥሮ ሳይንስ መስማት ለተሳናቸው ሁለቱም ፆታዎች የማለፊያ ነጥብ 350 ሲሆን በተፈጥሮ ሳይንስ ድጋሚ ተፈታኞች ማለፊያ ነጥብም 443 ሆኖ ተደርጓል።

በሁለተኛ ዙር የተፈተኑ እና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ለመከታተል ለሚፈልጉ የተፈጥሮ ሳይንስ መግቢያ ነጥብ ከ350 በላይ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ለማኅበራዊ ሳይንስ መደበኛ ተፈታኞች የማለፊያ ነጥብ ለወንድ 317፣ ለሴት 305 ሲሆን በማኅበራዊ ሳይንስ በታዳጊ ክልሎች እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ላሉ መደበኛ ተፈታኞች ደግሞ ለወንድ 305፣ ለሴት 300 ማለፊያ ነጥብ እንደሆነ ተገልጿል።

ለማኅበራዊ ሳይንስ መስማት ለተሳናቸው ሁለቱም ፆታዎች ማለፊያ ነጥብ 300 ሲሆን ለማኅበራዊ ሳይንስ ድጋሚ ተፈታኞች ደግሞ ለሁለቱም ፆታ የማለፊያ ነጥብ 335 ሆኗል።

በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ለመከታተል ለሚፈልጉ ደግሞ የማኅበራዊ ሳይንስ ከ300 በላይ ነጥብ ምግኘት ይጠበቅባቸዋል።

ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ ይህ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግቢያ ውጤት የተያዘው ለመጀመርያ ዙር ተፈታኞች ለተፈጥሮ ሳይንስ ከ600 እዲሁም ለማኅበራዊ ሳይንስ ከ500 ነው።

ለሁለተኛ ዙር ተፈታኞች ደግሞ ለተፈጥሮ ሳይንስ ከ700 እዲሁም ለማኅበራዊ ሳይንስ ከ600 የተያዘ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።