ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ የሩሲያን የአልማዝ ማዕድንና ቮድካ መጠጥ አገደች
አሜሪካ የሩሲያን ቮድካ ጨምሮ አልማዝና፣ የዓሣ ምርቶችን ወደ አገሯ እንዳይገቡ አገደች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ይህን እግድ ያስታወቁት ሩሲያ ላይ ተጨማሪ ምጣኔ ሀብታዊ ቅጣት እንጥላለን ያሉትን ቃል ተከትሎ ነው።
አሜሪካና የምዕራብ አጋር አገሮቿ ሩሲያን የአቻ አገር የንግድ ሸሪክ ከሚለው የንግድ ትስስር ሊፍቋት እንደሆነም እየተነገረ ነው።
ይህ እውን ከሆነ ሩሲያ ሌሎች ጥብቅ ምጣኔ ሀብታዊ ቅጣቶች ይጠብቋታል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአቻ አገር ንግድ ሸሪክ መሆን የታሪፍ ክፍያ ቅናሽን እንዲሁም ተደራራቢ ግብርን የሚያስቀር ነው።
ሩሲያ ይህን የንግድ ክብርና ሞገስ ስታጣ ገደብ ባልተጣለባቸው የውጭ ምርቶቿ ላይ ሳይቀር እጥፍ ድርብ ግብርና ታሪፍ ያስከትልባታል።
በዚህ ዕቀባ ላይ ካናዳ፣ ጃፓንና ሌሎች የአሜሪካ ሸሪኮች እንዲሳተፉ ባይደን ማግባባት ይዘዋል።
ምዕራባዊያን ከጦርነቱ ወዲህ በሩሲያ ላይ የጣሏቸው የንግድ ዕቀባዎች የአገሪቱን መገበያያ ገንዘብ በእጅጉ አንኮታኩቶታል።
ይህን ተከትሎም በርካታ ኩባንያዎች ሩሲያ እየለቀቁ በመውጣት ላይ ናቸው።
ማክዶናልድስ ባለፈው ሳምንት ጠቅልሎ ከመላው ሩሲያ መውጣቱ ይታወሳል።
ሞስኮ በበኩሏ በአገሪቱ ሥራ የሚያቆሙ ኩባንያዎችን መንግሥት ሊወርስ እንደሚችል አስጠንቅቃለች።
ቪላድሚር ፑቲን እነዚህ የምዕራብ አገራት ዕቀባዎች ከጦርነት ማወጅ አይተናነሱም ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ምዕራብ አገራት የፑቲን የቅርብ ሰዎች ናቸው ባሏቸው ቢሊየነሮች ላይም ዕቀባ እየጣሉ ሲሆን ከትናንት በስተያ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የቼልሲ እግር ኳስ ቡድን ባለቤት በነበሩት ሮማን አብራሞቪች ላይ ተመሳሳይ እርምጃን ወስዷል።
የአውሮፓ አገራት ትናንት ተሰብስበው ሩሲያ ላይ ተጨማሪ ቅጣቶች የሚጣሉበትን መንገድ ሲመክሩ ነበር።
ከዚህ ምክክር በኋላ ኅብረቱ የሩሲያ የግንባታ ብረት ምርቶች ላይ እንዲሁም የኃይል አቅርቦት ዘርፍ ላይ አዲስ ዕቀባን ጥሏል።
ዩናይትድ ኪንግደም በበኩሏ በመቶ በሚቆጠሩ የሩሲያ ፖለቲከኞች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና የአውሮፓ ኅብረት ከሩሲያ የሚመጡ ውድና የከበሩ ዕቃዎች ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።
ባይደን እነዚህ እርምጃዎች የሩሲያን ምጣኔ ሀብት የሚያንኮታኩቱ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።