ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰው ልጆች በሞት አፋፍ ላይ ሕይወታቸውን በብልጭታ ያዩታል
ከሳይንቲፊክ አክሲደንት የተገኙ አዳዲስ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሰው ልጆች በሞት አፋፍ ላይ ባሉባት ቅፅበት የኖሩትን ሕይወት በብልጭታ እንደሚያዩት ነው።
አንድ የሳይንስ ሊቃውንት ቡድን የሚጥል ሕመም ያለባቸውን የ87 ዓመት ታካሚ የአእምሮ ሞገድ ለመለካት ተነሳ።
ነገር ግን ምርምራውን በሚያካሂዱበት ወቅት የከፋ የልብ ድካም ያጋጠማቸው ሲሆን እየሞተ ያለ አእምሮም ምን ሊመስል እንደሚችል አሳይቷል።
ከሞት በፊትና በኋላ ያሉ 30 ሰኮንዶችን መመዝገብ የተቻለ ሲሆን የግለሰቡ የአእምሮ ሞገድም እንደሚያሳየው የሕይወታቸውን ሙሉ ትዝታዎችን ወይም ሕልሞች ማየት እንደቻሉ መዝግበዋል።
የዚህ ዓይነት የአእምሮ እንቅስቃሴ የመጨረሻ "የሕይወት ትውስታ" ሰዎች በሞት አፋፍ ላይ በሚሆኑበት ወቅት ሊከሰት እንደሚችል ሊጠቁም ይችላል ሲልም ቡድኑ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ 'ፍሮንቲየርስ ኢን ኤጂን ኒውሮሳይንስ' ላይ በወጣው ጥናታቸው ላይ አትተዋል።
የጥናቱ ተባባሪ ጸሐፊ ዶክተር አጅማል ዘማር እንደተናገሩት ቡድኑ በወቅቱ በካናዳ ቫንኩቨር ያደረገው ጥናት እየሞተ ያለ አእምሮ ምን ዓይነት ይመስላል በሚል በአጋጣሚ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ መሆኑን ነው።
"ይህ በእውነቱ የተገኘው በአጋጣሚ ነው። ይህንን ሙከራ ለማድረግ ወይም እንደዚህ ዓይነት ምልክቶችን ለመቅዳት የሚል ዕቅድ ይዘን አልጀርንም" ብለዋል።
የሰው ልጆች በሞት አፋፍ ላይ በሚሆኑበት ወቅት የሚወዷቸውን ሰዎች ትዝታ በጨረፍታ ያዩት ይሆን ወይስ ሌሎች አስደሳች ትዝታዎችን ማየት እንችላለን ለሚለው ጥያቄ ዶክተር አጅማል በአሁኑ ወቅት መናገር አይቻልም ይላሉ።
"ወደ ፍልስናው ዓለም ብንመጣ ይህችን ዓለም ለመሰናበት በቅፅበት ላይ ባለንበት ወቅት የሕይወታችን ትውስታ በብልጭታ የምናየው ከሆነ ከመጥፎ ነገሮች ይልቅ ጥሩ ትዝታዎችን የምናይ ይመስለኛል" ብለዋል።
"ነገር ግን የማይረሱ ትዝታዎች የምንላቸው ከሰው ሰው የተለያዩ ይሆናል" ሲሉ ያስረዳሉ።
በአሁኑ ወቅት በሉዊስቪል ዩኒቨርሲቲ የነርቭ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አጅማል እንዳሉት የታካሚው ልብ ለአንጎሉ ደም ማስተላለፍ ከማቆሙ በፊት ባሉት 30 ሰኮንዶች ውስጥ የተመዘገበው የአእምሮ ሞገድ እንደሚያሳየው ከፍተኛ የግንዛቤ ተግባራትን የሚጠይቁ አትኩሮት፣ ማለም፣ ወይም በትዝታዎች ውስጥ መመላለስ የመሰሳሉ ተግባራትን ስንፈጽም የሚያሳይ ተመሳሳይ አካሄድ ማሳየቱን ነው።
የታካሚው ልብ መምታት ካቆመ ከ30 ሰኮንዶች በኋላ ሲሆን ይህ የተመዘገበው ይህም ማለት ሕመምተኞች በይፋ ሞተዋል የሚባሉበት ቅፅበት ላይ ነው።
"ይህ ምናልባት በሕይወት ውስጥ ያጋጠሙን ትዝታዎች የመጨረሻ ትውስታ ሊሆን ይችላል። እናም ከመሞታችን በፊት በመጨረሻዎቹ ባሉት ሰኮንዶች ውስጥ በአእምሯችን ውስጥ በድጋሚ እናያቸዋለን" ይላሉ።
ጥናቱ በትክክል የሰው ልጆች መቼ ነው ሞቱ የሚባሉት ልብ መምታት ሲያቆም? ወይስ አንጎል ስራውን ሲያቆም? በሚለውም ላይ ጥያቄዎችን ያጭራል።
ሆኖም ዶክተር አጅማል እና ቡድናቸው በዚህ በተደረገ አንድ ጥናት ሰፊ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንደማይቻል አስጠንቅቀዋል።
በተለይም ጥናት የተደረገባቸው ሕመምተኛ የሚጥል በሽታ፣ አንጎላቸው ላይ የደም መፍሰስና እብጠት ስለነበረባቸውም ነገሮችን የበለጠ ያወሳስበዋል ይላሉ።
"አንድን ጥናት ለመመዝገብ ምቾት ተሰምቶኝ አያውቅም" ይላሉ ዶክተር አጅማል።
በአውሮፓውያኑ 2016 የተመዘገበውን ይህን ጥናት ትንታኔውን ለማጠናከር የሚረዱ ተመሳሳይ ጥናቶች ለዓመታት ቢፈልጉም ሊሳካ አልተቻለም።
ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2013 በጤናማ አይጦች ላይ የተደረገ ጥናት ተመሳሳይ ፍንጭ ሰጥቷል።
በዚያ ትንታኔ መሰረት ልክ በዶክተር አጅማል የሚጥል ሕመምተኛ ላይ እንደተገኘው መረጃ ሁሉም የአይጦቹ ልብ መምታት ካቆመ ከ30 ሰኮንዶች በኋላ በአእምሮ ላይ ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ ሞገዶች መመዝገባቸውን የአሜሪካ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል።
በጥናቶቹ መካከል ያለው ተመሳሳይነት "አስገራሚ" ነው ብለዋል ዶክተር አጅማል።
በአንድ ሰው ላይ የታየው የጥናት ውጤት መታተም በመጨረሻዎቹ የሕይወት ቅፅበቶች ላይ ለሚደረጉ ሌሎች ጥናቶች በር እንደሚከፍት ተስፋ ያደርጋሉ።
"በሞት መቃረብ ላይ ካለው ተሞክሮ ጀርባ ሚስጥራዊ እና መንፈሳዊ ነገር ያለ ይመስለኛል" የሚሉት ዶክተር አጅማል "ለእንደዚህ አይነት ግኝቶችም ነው ሳይንቲስቶች ጉጉት የሚያድርባቸው" ብለዋል።