አሜሪካ ህወሓት በአማራ ክልል ፈጽሟቸዋል የተባሉ ጥቃቶች አሳሳቢ ናቸው አለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ፈጽመዋቸዋል የተባሉት ጥቃቶች እጅጉን አሳሳቢ ናቸው አለ።
ይህ የአሜሪካ መንግሥት መግለጫ የወጣው ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ከጦር ወንጀሎች ጋር የሚተካከል ደርጊት ፈጽመዋል የሚል ሪፖርት ማውጣቱን ተከትሎ ነው።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ፤ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በሪፖርቱ ከህወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸው ተዋጊዎች ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ጨምሮ ፈጽሟቸዋል የተባሉት በደሎች እጅጉን አሳስቦኛል ብሏል።
የአሜሪካ መንግሥት በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚያደርሱትን የሰብዓዊ መብት ጥስት እንዲያቆሙ ጠይቆ፤ የባይደን አስተዳደር ተፈጽማዋል የተባሉ በደሎች ተመርምረው ጥፋተኞች ተጠያቂ መሆና አለባቸው የሚል ጽኑ አቋም እንዳለው ገልጿል።
የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ ቀደም በትግራዩ ጦርነት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም የአማራ ክልል ኃይሎች በሲቪሎች ላይ ፈጽመዋቸዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሳስቦኛል ብሎ ነበር።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጣው ሪፖርት ላይ የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ገብተው በቆዩባቸው ጊዜያት ከጦር ወንጀል ጋር የሚተካከሉ በሲቪሎች ላይ ግድያ እና የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ይፋ አደርጎ ነበር።
አምነስቲ የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ከተሞች የሚገኙ በርካታ ንጹሃን ሰዎችን ሆነ ብለው መግደላቸውን፣ ሴቶች እና ታዳጊዎችን አስገድደው በቡድን መድፈራቸውን እንዲሁም የግል እና የሕዝብ ንብረት ማውደማቸውን በሪፖርቱ አስታውቋል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ከህወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች በጭና እና ቆቦ ከተሞች እንዲሁም በአካባቢው በሚገኙ ስፍራዎች ላይ ጥቃት ያደረሱት ከነሐሴ 2013 ዓ.ም. አጋማሽ እስከ መስከረም 2014 ዓ.ም. መጀመሪያ ባሉት ጊዜያት ነው ብሏል።
በዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ የሆነው ህወሓት ግን ንጹሃንን ዒላማ አለማድረጉን ገልጾ በአከባቢዎቹ ተፈጽመዋል የባሉት ግድያዎች እና ፆታዊ ጥቃቶች ምርመራ እና የማጣራት ሊደረግባቸው ይገባል ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ከትግራይ የውጭ ጉዳዮች ፅ/ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ፤ መሰል ድርጊት በንጹሃን ላይ ተፈፅሞ ከሆነ ህወሓት ከተጎጂዎቹ ጎን በመቆም ተፈጸመ የተባለውን ድርጊት እንዲመረመር እና ያጠፉ አካላት ከሕግ ፊት ለማቅረብ ይሰራል ብሏል።
ከ15 ወራት በፊት በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተሸጋግሮ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን አስከትሏል።
በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑት የፌደራሉ መንግሥት ጦር፣ የአማራ ክልል ኃይሎች፣ የኤርትራ ሠራዊት እና የህወሓት ኃይሎች በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ ስለመሆናቸው በተለያዩ ወገኖች በተደጋጋሚ ሲከሰሱ ቆይተዋል።












