ዩክሬን ግጭት፡ ጆ ባይደን ፑቲን ዩክሬንን ለመውረር መወሰናቸው "እርግጥ ነው" አሉ

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ ወረራ ለመክፈት መወሰናቸው "እርግጥ መሆኑን" የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ተናገሩ።

ጆ ባይደን ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈፅመው ወረራ "በሚቀጥሉት ቀናት" ሊከሰት ይችላል ብለዋል።

ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት የአሜሪካ የስለላ ድርጅት የዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ የወረራው ኢላማ እንደምትሆን ባወጣው መረጃ ላይ ተመስርተው እንደሆነ ተናግረዋል።

ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬንን ለመውረር አቅዳለች መባሏን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።

ምዕራባውያን አገራት ሩሲያ ጥቃት ለመሰንዘር ምክንያት ለመፍጠር በዩክሬን ተገንጣይ ምሥራቃዊ ክልሎች የሐሰት ቀውስ ለመፍጠር እየሞከረች ነው ሲሉ ይከሳሉ።

በዩክሬን ውስጥ እና በድንበር አካባቢ ከ169 ሺህ እስከ 190 ሺህ የሩሲያ ሠራዊት አባላት እንደሚገኙ አሜሪካ ግምቷን አስቀምጣለች።

ይህ አሃዝ ራስ ገዝ በሆኑትና በምሥራቅ ዩክሬን በሚገኙት ተገንጣዮቹ ዶኔትስክ እና ሉሃንስክ ሪፐብሊክ የሚገኙትን በሩሲያ የሚደገፉ ተዋጊዎችን የሚያካትት ነው።

እነዚህ ክልሎች እአአ በ1922 ወደ ዩክሬን የተጠቃለሉ ሲሆን አብዛኞቹ ነዋሪዎች የመጀመሪያ ቋንቋቸው ሩሲያኛ ነው።

ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከዋይት ሐውስ በቴሌቪዥን በተላለፈው መግለጫቸው አሜሪካ የሩሲያ ኃይሎች በሚቀጥለው ሳምንት ዩክሬንን ለማጥቃት እቅድና ፍላጎት እንዳላቸው ለማመን የሚያስችል "በቂ ምክንያት" አላት ብለዋል።

ባይደን አክለውም "ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ፑቲን ውሳኔውን መወሰኑን አምኛለሁ" ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ፐሬዚደንቱ እና ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልትወስድ ስለምትችለው እርምጃ በእርግጠኝነት እንደማያውቁ ተናግረው ነበር።

ሆኖም ፕሬዚደንት ባይደን ሩሲያ አሁንም ዲፕሎማሲያዊ መንገድን ልትመርጥ ትችላለች በማለት ውጥረቱን ለማርገብ እና ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለመመለስ አሁንም አለመርፈዱን ገልጸዋል።

አርብ ዕለት ውጥረቱ እየጨመረ በመምጣቱ የሁለቱ ተገንጣይ አካባቢ መሪዎች ዩክሬን ድብደባ ለመፈፀምና ጥቃት ለማድረስ አቅዳለች በማለት ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ አስታውቀው ነበር።

ይሁን እንጂ ዩክሬን ጥቃት የማድረስ እቅድ እንደሌላት በተደጋጋሚ ገልጻለች።

የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚይትሮ ኩሌባ "ይህ የሩሲያ የሐሰት መረጃ ነው" ሲሉም ክሱን አጣጥለውታል።

የዶኔትስክ ሕዝቦች ሪፐብሊክ መሪ የሆኑት ዴኒስ ፐሺሊን፣ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ያሳሰቡት አርብ ዕለት በወጣ ተንቀሳቃሽ ምሥል አማካይነት ነው።

ይሁን እንጂ ቢቢሲ ባደረገው የመረጃ ማጣራት ተንቀሳቃሽ ምሥሉ የተቀረጸው ከውጥረቱ መባባስ ከሁለት ቀናት በፊት መሆኑን ለማወቅ ችሏል።

ዩክሬን፤ ፕሬዚደንት ፑቲን ከተገንጣይ አካባቢዎች ለሚፈልሱ ሰዎች የአደጋ ጊዜ እርዳታ ለማቅረብ በድንበር አቅራቢያ የስደተኞች መጠለያ እንዲቋቋሙ ማዘዛቸውን ገልጻለች።

በርካታ የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች የጫኑ አውቶብሶችም ወደ ሩሲያ ማምራታቸውን የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መነገሩ ሩሲያ ጥቃቱን ለመሰንዘር ኃይሏን እያጠናከረች ላለው ዝግጅት ዓለምን ለማዘናጋት የተደረገ " የሞስኮ አሳፋሪ እርምጃ " ነው ብሎታል።

ዋይት ሐውስ ነዋሪዎችን እንዲወጡ ማድረግ ሞስኮ ሐሰተኛ መረጃን ለጦርነት ሰበብ መጠቀሟን የሚያሳይ ምሳሌ ነው ብሏል።