ቢሊየን ዓመት ያስቆጠረው ጥቁር አልማዝ በ4.3 ሚሊየን ዶላር ተሸጠ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለማችን ትልቁ የተቆረጠ አልማዝ ነው ተብሎ የሚታመነውና የቢሊየን ዓመት ዕድሜ ያለው ጥቁር አልማዝ በ4.3 ሚሊየን ዶላር ተሸጠ።
ዘ ኢኒግማ ተብሎ የተሰየመው የ555.55 ካራት አልማዝ ከአንድ ሙዝ ክብደት ጋር ተነጻጽሯል።
በበይነ መረብ ግብይትም ከ4.4 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ከአስትሮይድ ጋር ወደ ምድር መምጣቱን ጨምሮ ስለ አልማዙ አመጣጥ ብዙ መላ ምቶች አሉ።
አጫራቹ ሶዝባይ እንዳለው፤ ገዢው ክፍያውን በክሪፕቶከረንሲ ለማድረግ መርጧል።
ሶዝባይ የገዢውን ማንነት ሳይገልጽ ቆይቶ፤ ከጨረታው በኋላ የክሪፕቶከረንሲ ባለሙያው ሪቻርድ ኸርት የዘ ኢኒግማ ገዢ መሆኑን በማኅበራዊ ገጹ ገልጿል።
ሶዝባይ ከ180,000 በላይ ለሚሆኑት የትዊተር ተከታዮቹ፤ የአልማዙ ክፍያ እንደተጠናቀቀ እና ንብረቱን እንደተረከበ አልማዙ ሄክስ.ኮም ዳይመንድ (HEX.com Diamond) የሚል ስያሜ እንደሚሰጠው ገልጿል።
ስያሜው የክሪፕቶከረንሲ ባለሙያው ሪቻርድ ከመሠረተውን ብሎክቼይን የተገኘ ነው።
አልማዙ ካርቦንዶስ ነው ተብሏል። ይህም በጣም ጠንካራ ከሆኑ የተፈጥሮ አልማዞች አንዱ ነው።
ካርቦናዶስ የሚባሉት የአልማዝ አይነቶች ጥቂት ሲሆኑ አልፎ አልፎ የተገኙትም በብራዚል እና በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ብቻ ነው።
በሜትሮዎች ውስጥ ብቻ የሚገኘው ኦስቦርኔት የተባለውን ማዕድን ስላላቸው ከጠፈር እንደመጡ ይታመናል።
ሶዝባይ ዘ ኢኒግማን "በሰው ልጅ ዘንድ ከሚታወቁት ብርቅዬ፣ ከቢሊየን ዓመታት በላይ ካስቆጠሩት የጠፈር ድንቅ ስጦታዎች አንዱ ነው" ሲል ገልጾታል።
የጥቁር አልማዝ ትክክለኛ አመጣጥ በምስጢር የተሞላ ነው።
ጥቁር አልማዞች ከ2.6 እስከ 3.2 ቢሊየን ዓመታት መኖራቸው ይገመታል። ይህም ዳይኖሰር ከመፈጠሩ በፊት መሆኑ ነው።












