የፈረንሳዩ ማክሮን የሩሲያና ዩክሬንን ፍጥጫ ለማርገብ እየጣሩ ነው

ታትሟል

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መጪዎቹ ቀናት እጅግ ወሳኝ ናቸው አሉ፡፡

ማክሮን ይህን ያሉት ትናንት ሰኞ ከሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለሰዓታት የቆየ ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው፡፡

ማክሮን ከፑቲን ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬ እንደሚያፈራ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ምዕራብ አገራት ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር ዝግጅቷን ጨርሳለች በሚል በአካባቢው ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል መናገር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

አንዳንድ ከአሜሪካ ምድር የሚወጡ መረጃዎች ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር ከሚያስችላት ወታደራዊ አቅም 70 ከመቶውን ወደ ድንበር ማስጠጋቷን እየገለጡ ነው፡፡

አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ሩሲያ መቶ ሺህ የታጠቁ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ድንበር አስጠግታ ማስፈሯን ተናግረዋል፡፡

ሩሲያ ግን ምንም ዓይነት የወረራ ፍላጎት የለኝም ብላለች፡፡

ሰኞ ዕለት የአሜሪካኑ ጆ ባይደን ከጀርመኑ መራሒ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ጋር በዋሺንግተን ተገናኝተው በሩሲያ ጉዳይ ላይ በዝግ መክረዋል፡፡

ጆ ባይደን ለሩሲያ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ የሰጡ ሲኾን እንደተፈራው ፑቲን ዩክሬንን በወረራ ለመያዝ ከሞከሩ ሩሲያ ወደ ጀርመን የዘረጋችውን የጋዝ መስመር እንደሚዘጉ ዝተዋል፡፡

የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ፑቲን አይተውና ሰምተው የማያውቁት ዓይነት ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

ቦሪስ ጆንሰን ለዘታይምስ ጋዜጣ በጻፉት መጣጥፍ እንዳሉት በዩክሬን ላይ ወረራ ከተፈጸመ አገራቸው ዩኬ የሮያል አየር ኃይልን ብቻም ሳይኾን የባሕር ኃይሏንም ጭምር በአካባቢው እንደምታሰማራ አረጋግጠዋል፡፡

ዩኬን ጨምሮ ምዕራብ አገራት ዩክሬንን ከወረራ ለማዳን ያላቸውን አቅም ሁሉ እያስተባበሩ ይገኛሉ፡፡

ሩሲያ በበኩሏ እንዲያ ያለ ሐሳብ እንደሌላት ብትጎተጉትም ቁልፍ የደኅንነት ስጋቶቿ እንዲቀረፉላት ግን ትሻለች፡፡

ከነዚህ መካከል ዋንኞቹ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) ወደ ምሥራቅ አውሮጳ የሚያደርገውን መስፋፋት እንዲያቆም፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዩክሬንን በአባልነት የማካተት ሐሳቡን እርግፍ አድርጎ እንዲተው የሚሉ ናቸው፡፡

ትናንት ወደ ሞስኮ ያቀኑት የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን ከፑቲን ጋር ለአምስት ሰዓታት ያህል የእራት ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ቆይታቸው ተስፋ ሰጪ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

ማክሮን ከፑቲን ጋር በነበራቸው ዘለግ ያለ የእራት ሰዓት ውይይት የአጋዘን ሥጋ፣ ስኳር ድንችና ብላክቤሪ ጭምር እንደተቋደሱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ፑቲን በበኩላቸው ከእራት ግብዣው በኋላ በሰጡት አጭር አስተያየት የማክሮን ነጥቦች ሊዳብሩ የሚችሉና ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል፡፡

ኾኖም ዝርዝር ጉዳዮችን ለመናገር ጊዜው ገና ነው ሲሉ አስተያየታቸውን በአጭር ቋጭተዋል፡፡

ማክሮንና ፑቲን የሁለትዮሽ ውይይታቸውን ነገ የሚቀጥሉ ሲሆን ይህም የሚሆነው ማክሮን ወደ ኪያቭ አቅንተው የዩክሬኑን አቻቸውን አነጋግረው ሲመለሱ ነው፡፡

ሩሲያ ከምታነሳቸው የደኅንነት ስጋቶች አንዱና ዋንኛው ዩክሬን ኔቶን ከተቀላቀለች ክሬሚያን ለማስመለስ ታልማለች የሚል ነው፡፡

ሩሲያ የክሬሚያን ባሕረ ገብ ግዛት በወረራ የወሰደችው የዛሬ ስምንት ዓመት ግድም ነበር፡፡

ፑቲን ከሁለትዮሹ ንግግር በኋላ በአቅራቢያቸው ለተሰበሰቡ የፈንሳይ ጋዜጠኞች፣ ‹ፈረንሳይ ከሩሲያ ጋር እንድትዋጋ ትሻላችሁን?› ሲሉ ድንገቴ ጥያቄ የሰነዘሩላቸው ሲሆን፣ ‹ጦርነት ከተጀመረ ማንም አሸናፊ አይሆንም› ሲሉ ያልተጠበቀ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ይህ በአንዲህ ሳለ አዲሱ የጀርመን መራሒ መንግሥት ሾልዝ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ዋሺንግተን አቅንተው ከባይደን ጋር በሩሲያ ጉዳይ መክረዋል፡፡

ሩሲያ ዪክሬንን ከወረረች ፍጹም የማትቋቋመው ብቻ ሳይሆን አከርካሪዋን የሚሰብር ማዕቀብ ይጠብቃታል ሲሉም ዝተዋል፡፡

ባይደን በበኩላቸው ፑቲን ወረራ ከፈጸሙ ኖርድ ስትሪም2 ተብሎ የሚጠራውንና ወደ ጀርመን የተዘረጋውን የጋዝ መስመር እንደሚያቆሙት ዝተዋል፡፡

የዚህ መስመር መዘጋት ሩሲያን እንደሚጎዳት ሁሉ አውሮጳዊያኑንም በኃይል አቅርቦት በእጅጉ ይጎዳል ይላሉ ተንታኞች፡፡

ጆ ባይደን ይህን እንዴት ያሳካሉ ተብለው ሲጠየቁ በቀጥታ ለመመለስ ባይችሉም ለጋዜጠኞች፣ ‹እመኑኝ እናደርገዋለን› ሲሉ በድፍኑ ዝተዋል፡፡

ከ1ሺህ 225 ኪሎ ሜትር በላይ የተዘረጋው የኖርድ ስትሪም2 የጋዝ መስመር ከሞስኮ ወደ ጀርመን የሚደርስ ነው፡፡

መስመሩን ለመዘርጋት ድፍን 5 ዓመት የወሰደ ሲሆን 11 ቢሊዮን ዶላር ወጥቶበታል፡፡ ሆኖም እስከዛሬ ሥራ አልጀመረም፡፡

እንደተፈራው በሩሲያና በዩክሬን መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮጳ ምድር የሚደረግ ሰፊ ጦርነት ሊሆን ይችላል ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡