ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የስፔኗ ካታሎኒያ በጥንቆላ ተወንጅለው ለተገደሉ ሴቶች ምህረት አደረገች
የካታላን ክልል ፓርላማ በአውሮፓውያኑ 15ኛው እና 18ኛው ክፍለ ዘመን በጥንቆላ ተወንጅለው ለተገደሉ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች በይፋ ምህረት አድርጋለች።
ከ700 በላይ የሚሆኑ ሴቶች በጥቆላ ተወንጅለው ተሰቃይተው የተገደሉ ሲሆን የፓርላማ አባላቱም ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት የሴቶቹን ታሪክ በመልካም መልኩ ለመዘከር ነው።
የስፔን ታሪክ ተመራማሪዎች ካታሎኒያ በአውሮፓ ውስጥ ጠንቋይ የተባሉ ሴቶችን በማደን የመጀመሪያዎቹ አንዷ እንደነበረችም በጥናታቸው ደርሰውበታል።
የካታሎን ግዛት በጥንቆላ የተወነጀሉትም የሞት ቅጣት በከፋ ሁኔታ ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች አንዳ እንደሆነችም ይነገራል።
"በ15ኛው እና 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መካከል የተሳደደዱ፣የተሰቃዩ እና በግፍ የተገደሉ ከ700 በላይ ሴቶችን ስም በቅርቡ አግኝተናል።" ሲሉ ውሳኔውን ያሳለፈው የፓርላማ አባላት ቡድን አስታውቋል።
እነዚህ በጥንቆላ የተወነጀሉ ሴቶች ለህፃናት ድንገተኛ ሞት ወይም ለቀነሰ ምርት ምክንያት ተጠያቂ ይሆኑ እንደነበር በባርሴሎና ዩኒቨርሲቲ የዘመናዊ ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ፓው ካስቴል ተናግረዋል።
የነጻነት ደጋፊ እና የግራ ክንፍ ቡድኖች ሴቶቹ "በፆተኝነት ላይ የተመሰረተ ጥቃት ደርሶባቸዋል" ሲሉም በሴቶቹ ስም ጎዳናዎችን በመሰየም እንዲታሰቡ እና ትዝታቸውም በበጎ እንዲከበር ይፈልጋሉ።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው ሴቶች በመላው አውሮፓ በጥንቆላ ተወንጅለው የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል ተብሎ ይታመናል።
በስኮትላንድ፣ ስዊዘርላንድ እና ኖርዌይ ተመሳሳይ እርምጃዎችም ተወስደዋል።
"ቀድሞ ጠንቋዮች ብለው ይጠሩን ነበር አሁን ደግሞ 'ፌሚናዚስ' ወይም በወሲባዊ ግንኙነት የተበሳጩ እያሉ ይጠሩናል።ድሮ ጠንቋይ እያደንን ነው እያሉ ይገድሉ ነበር አሁን ደግሞ ዝም ብሎ ሴትን ወደ መግደል 'ፌምሳይድ' ተቀይሯል" ሲሉ የ የክልሉ ገዢው ፖርቲ ኢአርሲ ምክትል ጄን ዲያዝ ለኤኤፍፐ የዜና ወኪል ተናግረዋል።